ከግብፅ ጋር የተደረገው ስምምነት የኢትዮጵያን ጥቅም ለመጉዳት ያለመ አይደለም ሲል የሱዳን መንግስት አስታወቀ

ኢሳት (ጥር 10 ፥ 2009)

የደቡብ ሱዳን መንግስት በቅርቡ ከግብፅ ጋር ያደረግነው ስምምነት የኢትዮጵያን ጥቅም ለመጉዳት ያለመ አይደለም ሲል አስተባበለ።

መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉት የሃገሪቱ አምባሳደር ጀምስ ፒታ-ሞርጋ ፕሬዚደንት ሳል-ቫኪር በግብፅ ያደረጉት ጉብኝት የተለመደና በሁለቱ ሃገራት ትብብር ዙሪያ ለመምከር ያለመ እንደነበር ለኢትዮጵያ ቴለቪዥን በሰጡት ቃለምልልስ ገልጸዋል።

ይሁንና የደቡብ ሱዳን መገናኛ ብዙሃን የሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ዋቢ በማድረግ የግብጹ ፕሬዚደንት አብደል ፈታህ አልሲሲ እና ሳልባ-ኪር ግብፅ በአባይ ወንዝ ፍሰት ላይ ስላላት መብትና ጥቅም ዙሪያ መምከራቸውን መዘገባቸው ይታወሳል።

ከአንድ ሳምንት በፊት በካይሮ የመከሩት ሁለቱ ፕሬዚደንቶች ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ ያላት የቆየ ስምምንት ዘላቂ በሚሆንበት ዙሪያ መምከራቸውም ተመልክቷል።

ይሁንና በጉዳዩ ዙሪያ ለኢትዮጵያ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ቃለምልልስን የሰጡት የደቡብ ሱዳን አምባሳደር በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲሰራጭ የቆየውን የሁለቱ ወገኖች የተጋነነ እና ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ አስተባብለዋል።

ሁለቱ ሃገራት ግን ውይይቱን አስመልክቶ እስካሁን ድረስ በይፋ የሰጡት ምላሽ የሌለ ሲሆን፣ ስምምነቱ ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ያሻክራል ተብሎ ተሰግቷል።

የደቡብ ሱዳን መንግስት ባለስልጣናት ኢትዮጵያ የአማጺ ቡድንን ትደግፋለች ሲሉ በተደጋጋሚ ቅሬታን ሲያቀርቡ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ሁለቱ ሃገራት ከወራት በፊት አንደኛው ሃገር የሌላኛውን ተቃዋሚ ላለመደገፍ ስምምነት መፈጸማቸው የሚታወስ ነው።

በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን መንግስታት መካከል የተፈረመውን ይህንኑ ስምምነት ተከትሎ ኢትዮጵያ የአማጺ ቡድን መሪው ሪክ ማቻር ወደ ሃገሯ እንዳይገቡ እገዳን ጥላ ትገኛለች።

ኢትዮጵያና ግብጽ በአባይ ግድብ ዙሪያ ያላቸውን ልዩነት ለማስወገድ ባለፉት ሶስት አመታት ድርድርን ሲያካሄዱ ቢቆዩም ድርድሩ እስካሁን ድረስ ውጤት አለማምጣቱ ይታወቃል።

ይሁንና ሁለቱ ሃገራት ተቋርጦ የቆየውን ይህንኑ ውይይት ለመቀጠል በቅርቡ ፍላጎትን ያሳዩ ሲሆን፣ በቀጣዩ ሳምንት በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ልዩ የመሪዎች ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያና ግብጽ ባለስልጣናት በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።