ኢሳት (ጥር 10 ፥ 2009)
የናይጀሪያ አየር ሃይል በአንድ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ላይ በስህተት ፈጽሞታል በተባለ የአየር ጥቃት ከ50 የሚበልጡ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።
ሃገሪቱ ከጎረቤት ካሜሮን ጋር በሚያዋስናት የድንበር አካባቢ በጦር አውሮፕላን የተፈጸመው ይኸው ጥቃት ቦኮ ሃራም ተብሎ በሚጠራው ታጣቂ ሃይል ላይ ሊካሄድ የነበረ ጥቃት እንደነበር የናይጀሪያ አየር ሃይል ይፋ ማድረጉን CNN ዘግቧል።
ይሁንና ጥቃቱ ራን ተብሎ በሚጠራ ከተማ በሚገኝ አንድ የስደተኛ ጣቢያ ላይ በመፈጸሙ ንጹሃን ሰዎች መሞታቸውንና ከ100 የሚበልጡ ተጨማሪ ሰዎችም ጉዳት እንደደረሰባቸው ተመልክቷል።
በመጠለያ ጣቢያው በታጣቂ ሃይሉ ጥቃት የተፈናቀሉ ወደ 25ሺ አካባቢ ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን፣ የዕርዳታ ሰራተኞች ጭምር የዚሁ ጥቃት ሰለባ መሆናቸውን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የናይጀሪያ አየር ሃይል በበኩሉ የስደተኛ ጣቢያው የታጣቂ ሃይሉ ቦኮ ሃራም ማሰልጠኛ ተቋም መስሎ በመታየቱ የአየር ጥቃቱ ሊፈጸምበት መቻሉና የሟቾቹ ቁጥርም እየተጣራ መሆኑ አስታውቋል።
በአየር ጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በርካታ በመሆናቸውና የህክምና አገልግሎቱ የተሟላ ባለመሆኑ የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
የአለም ቀይ መስቀል ማህበር በአየር ጥቃቱ በናይጀሪያ ቀይ መስቀል ስር የሚሰሩ ስድስት አባላቱ መገደላቸውንና 13 ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቋል።
በስህተት ጥቃት ተፈጽሞበታል በተባለው የስደተኞቹ መጠለያ ጣቢያ ሁለት ተዋጊ አውሮፕላኖች ተከታታይ የአየር ጣት ማካሄዳቸውን የአይን እማኞች ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
የሃገሪቱ ፕሬዚደንት ሙሃመድ ቡሃሪ ተፈጥሯል ባሉት ስህተት ከፍተኛ ድንጋጤ እንደተሰማቸው በመግለጽ ድርጊቱ ምርመራ እንደሚካሄደበት ተናግረዋል።
ይሁንና የተለያዩ አካላት ከ25 ሺ በላይ ስደተኞችን በያዘ ጣቢያ ላይ እንዲህ ያለ ስህተት እንዴት ሊፈጸም እንደቻለ ግልጽ አለመሆኑን እየገለጹ ሲሆን፣ ስፍራው በናይጀሪያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር የሚገኝ እንደሆነ ተነግሯል።
በሰሜን ምስራቅ ናይጀሪያ በተፈጸመው በዚሁ ጥቃት የናይጀሪያ ወታደሮች ከሟቾች መካከል ሊሆኑ እንደሚችል ተገምቷል።
ከሰባት አመት በፊት የትጥቅ ትግሉን የጀመረው ቦኮ ሃራም፣ በናይጀሪያ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት የሚታገል እንደሆነ የሚገልጽ ሲሆን፣ ምዕራባዊ ትምህርትን አጥብቆ እንደሚቃወምም ይነገርለታል።
ታጣቂ ሃይሉ ከ20ሺ በላይ ለሚሆኑ ናይጀሪያዊያን ሞት ምክንያት መሆኑንም የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።