ጥር ፱ ( ዘጠኝ )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ላለፉት ሰባት ዓመታት የሀገርና የመንግሥት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለለስልጣናት፣ የፓርላማ አባላትና ዳኞች በተለያዩ ምክንያቶች ከኃላፊነታቸው ሲነሱ የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችና መብቶችን በአዋጅ ቁጥር 653/2001 አማካይነት ሲያገኙ የቆዩ ቢሆንም፣ ዛሬ ማክሰኞ፣ ጥር 9 ቀን 2009 ዓም ለፓርላማው የቀረበው አዋጅ በተለይም የሚኒስትሮች፣ የሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የምክትል ሚኒስትሮች የመቋቋሚያ አበል፣ የሥራ ስንብት ክፍያ፣ የመኖሪያ ቤትና የትራንስፖርት(የተሸከርካሪ) አበል ጥቅሞች በእጥፍ ያሳድጋል።
ይህ ረቂቅ አዋጅ ለመንግሥት ሠራተኞች ከጥር 1 ቀን ጀምሮ ሊጨምር ካሰበው ደመወዝ ጋር ተያይዞ ለፓርላማው ከቀረበው የበጀት ማሻሻያ ረቂቅ ጋር ተያይዞ እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን፣ ይህን ለማድረግ የታሰበውም ጫጫታ እንዳይፈጠር ተብሎ ሊሆን እንደሚችል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል። መንግሥት በዋነኝነት በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የተካሄዱ ሕዝባዊ የተቃውሞ ንቅናቄዎች ድንጋጤ ካስከተለበት በኃላ የመንግሥት ሠራተኞችን ደመወዝ ለመጨመር በፕሬዚደንት ሙላቱ ተሾመ በኩል ቃል የገባው በዚህ ዓመት መስከረም ወር ማብቂያ በፓርላማ መክፈቻ ስነስርኣት ላይ ነበር።
ኢህአዴግ መራሹ መንግሥት፤ የመንግስትን ሥልጣን ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት መኖራቸውን በማመን በጥልቅ ተሀድሶ “ራሴን አጠራለሁ” ብሎ ባለበትና አንዳንድ ሚኒስትሮችና ሹማምንትን ከሃላፊነት ባነሳበት በዚህ ወቅት፣ ከስልጣናቸው የሚሰናበቱ ሹማምንትን በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቅም አዋጅ ማውጣቱ አስገራሚ መሆኑንም ጠቅሷል።
በሌላ ዜና የመንግሥት ሠራተኞችን ደመወዝ ጨምሮ ለወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ እና ለድርቅ ችግር የሚውል የ18 ቢሊየን ተኩል ተጨማሪ በጀት ለፓርላማ ቀርቦ ዛሬውኑ በአፋጣኝ እንዲጸድቅ ሆኗል፡፡ ከዚህ በጀት ውስጥ ዘጠኝ ቢሊየን ብሩ ለመንግስት ሠራተኞች ደመወዝ ጭማሪ የተያዘ ነው፡፡ ለ2009 በጀት ዓመት ተይዞ የነበረው 274 ቢሊየን ብር በጀት የ36 ቢሊየን ብር ጉድለት ይታይበታል፡፡ የአሁኑ ተጨማሪ በጀት በሀገር ውስጥ ገቢ ለመሸፈን መታቀዱ ቢገለጽም፣ ቀደም ብሎ የታየውን የበጀት ገድለት ወደ 50 ቢሊዮን ብር ከፍ ያደርገዋል።
ጭማሪውን ተከትሎ እንደመኖሪያ ቤት ኪራይ እና አንዳንድ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ንረት ተከስቶ ሠራተኛው ከድጡ ወደማጡ እንዳይገባ የብዙዎች ስጋት ሆኖአል፡፡