(ጥር 9 ፥ 2009)
ኬንያ ባለፈው አመት በሶማሊያ በሚገኘው አንድ የጦር ማዘዣ ጣቢያዋ ላይ በተፈጸመ ጥቃት 173 ወታደሮቿን ማጣቷን ይፋ አደረገች።
ሃገሪቱ በአልሸባብ ታጣቂ ሃይል የደረሰባትን ጉዳት ለመገናኛ ብዙሃን ግልጽ ከማድረግ ተቆጥባ ብትቆይም የኬንያ ወታደራዊ ባለስልጣናት በጥቃቱ 173 ወታደሮች መሞታቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ማሳወቃቸውን ዘስታንዳርድ የተሰኘ የሃገሪቱ ጋዜጣ ማክሰኞ ዘግቧል።
በሶማሌ ኤል አዴ ተብሎ በሚጠራው የኬንያ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ ላይ ጥቃቱ በተፈጸመ ጊዜ 234 የሚሆኑ የኬንያ ወታደሮችና ወታደራዊ ሃላፊዎች በጣቢያው እንደነበሩ ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ እና ከጥቃቱ የተረፉ ወታደሮች አስረድተዋል።
አልሸባብ የተሰኘው ታጣቂ ሃይል በውድቅት ሌሊት በማዘዣ ጣቢያው ላይ ጥቃቱን ለማድረግ ወደ 2ሺ አካባቢ የሚጠጉ ታጣቂዎችንና በቦምብ የተሞሉ ተሽከርካሪዎችን አሰማርቶ እንደነበርም አመልክቷል።
ሰዓታትን ፈጅቷል በተባለው በዚሁ የሁለቱ ወገኖች ግጭት ከታጣቂ ሃይሉ ወደ 500 የሚጠጉት መሞታቸውን እና 13 የኬንያ ወታደሮችም በአልሸባብ ተይዘው መወሰዳቸውን እማኞችን ዋቢ በማድረግ ጋዜጣው አስነብቧል።
በአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሃይል ስር ወታደሮችን አሰማርተው የሚገኙ ሃገራት በታጣቂ ሃይሉ የሚሞቱባቸውን ወታደሮች ቁጥር ለህዝባቸው ይፋ ከማድረግ ተቆጥበው እንደሚገኙም ታውቋል።
የሰላም አስከባሪ ሃይሉ ከሃገሪቱ ፈቃደኝነት ውጭ የሚሞቱ ወታደሮችን ቁጥር ይፋ እንደማያደርግ የኬንያ ወታደሮች ለጋዜጣው በሰጡት ቃለምልልስ ገልጸዋል።
ሰሞኑን ኬንያ የሞቱባትን ወታደሮችን ለመዘከር በተዘጋጀ አንድ ስነስርዓት ላይ የ173ቱ ሟች የኬንያ ወታደሮች ቤተሰቦች ሁኔታውን አስመልክተው ለመገኛኛ ብዙሃን ማረጋገጫን እንደሰጡም ለመረዳት ተችሏል።
ይሁንና ስማቸው ይፋ እንዳይደረግ የፈለጉ ወታደራዊ ሃላፊዎችና ከጥቃቱ የተረፉ ወታደሮች ከዘስታንዳርድ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የዛሬ አንድ አመት በተፈጸመው በዚሁ ጥቃት 173 የኬንያ የሰላም አስከባሪ አባላት መሞታቸውን አረጋግጠዋል።
ጥቃቱ ከፈጸሙ የአልሸባብ አባላት መካከል የኬንያ እና የሌሎች አፍሪካ ሃገራት ብሄራዊ ቋንቋ የሆነውን ስዋሂሊ በአግባቡ እንደሚናገሩና በታጣቂ ሃይሉ ውስጥ የኬንያ ተወላጆች ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ጥርጣሪ ማሳደሩንም የኬንያ ወታደራዊ ሃላፊዎች አክለው ገልጸዋል።
ታጣቂ ሃይሉ በኬንያ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ ላይ ከደረሰው ጥቃት በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት ተመሳሳይ ጥቃቶችን በኢትዮጵያ ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ መፈጸሙ ይታወሳል።
ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ የአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ሃይሉ በጥቃቱ ሰለደረሰው ጉዳት የሰጡት መረጃ የሌለ ሲሆን፣ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሶስት ይዞታዎች ለቀው መውጣታቸውንም ሲዘገብ ቆይቷል።