ጥር ፰ (ስምንት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢትዮጵያ ብር ከአሜሪካን ዶላር ጋር ሲነጻጻር የመግዛት አቅሙ በተከታታይ እያሽቆለቆለ መምጣት ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካፒታሉን ወደ 40 ቢሊየን ብር ለማሳደግ ተገዷል።
ለፓርላማው ሰሞኑን የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ባንኩ በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ቢያደርግም ካፒታሉ ከአጠቃላይ የንብረት ዕድገቱ ጋር ሲተያይ በተመጣጣኝ መልኩ አላደገም፡፡ በመሆኑም በመንግሥት ዕዳ ሰነድ ወይንም ቦንድ አማካይነት የ26 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ለባንኩ ካፒታል ማሳደጊያ እንዲውልና ገንዘቡም ከአምስት ዓመታት የችሮታ ጊዜ በኋላ በ10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ እንዲከፍል ይደነግጋል፡፡
ንግድ ባንክ ተጨማሪ ካፒታል ከጠየቀባቸው ምክንያቶች መካከል የኢትዮጵያ ብር ከዶላር ጋር ሲነጻጸር በየዓመቱ በአማካይ የ5 በመቶ የዋጋ መቀነስ ወይንም መውደቅ አንዱና ዋንኛው ምክንያት ነው ተብሏል፡፡ በተጨማሪም በብሔራዊ ባንክ የተቀመጠው የውጭ ምንዛሪ ዕዳ እና የንብረት ክፍተት መጠበቅ አለመቻል እና ከውስብስብ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ከጊዜ ወደጊዜ የባንኩ አሠራር ለአደጋ ተጋላጭነቱ እየጨመረ መምጣት ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ረቂቅ አዋጁን ለማብራራት ከባንኩ የወጣ ሰነድ እንደሚጠቅሰው አጠቃላይ የብር ዋጋ ሪፖርት የሚደረገው ዋጋውን በማያሳይ ምጣኔ (Nominal rate) ሲሆን ይህም የምጣኔ አንድ አሀድ የውጭ ገንዘብ ከሌላው ጋር በምን ያህል
መጠን ሊለወጥ እንደሚችል ያሳያል፡፡ በዚህ ረገድ የአሜሪካን ዶላር ባለው ዓለምቀፋዊ ተቀባይነት የተነሳ የኢትዮጵያ ብር ከአሜሪካ ዶላር ጋር በመቆራኘት ይገለጻል፡፡
ግምገማው በተካሄደባቸው ዓመታት የኢትዮጵያ ብር ከአሜሪካ ዶላር ጋር ሲነጻጸር የዋጋ መቀነስ አሳይቷል፡፡ እ.ኤ.አ በ2009 አንድ የአሜሪካን ዶላር በብር 11 ነጥብ ከ40 ሳንቲም ይመነዘር የነበረው እ.እ.አ በ2015 የምንዛሪ መጠን ወደ 20 ብር ከ7 ሳንቲም ማሻቀቡን ይገልጻል፡፡ የባንኩ ጠቅላላ ንብረት እ.ኤ.አ በሰኔ ወር 2015 ዓ.ም 303 ቢሊየን ብር የነበረ ሲሆን አጠቃላይ የተከፈለ ካፒታሉ 13 ቢሊየን ብር እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በ2007 ዓ.ም የተጠናቀቀው የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንሰፎርሜሽን መርሃግብር ከኤክስፖርት ዘርፍ 10 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት አቅዶ የነበረ ቢሆንም በተጠቀሰው ዓመት የተገኘው ገቢ ግን ከ3 ቢሊየን ዶላር ያነሰ ሆኖ መገኘቱ የሚታወስ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም መንግሥት ካጋጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተያይዞ የውጭ ምንዛሪ ለሚጠይቁ ላኪዎች በወረፋና እንደተሰማሩበት ዘርፍ አስፈላጊነት እየታየ የሚያገኙበት አሠራር ተግባራዊ መደረጉ ኦኮኖሚውን ይበልጥ እያደቀቀው ነው።
ለፓርላማው የቀረበው ይህ ረቂቅ አዋጅ የበጀትና የፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮምቴ በዝርዝር እንዲመለከተው ተመርቶለታል፡፡