ጥር ፰ (ስምንት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የደቡብ ኦሞ ዞን አገር ሽማግሌዎች “ በህይወት ዘመናችን አይተነው የማናውቀውና የዞኑ ከተማ ጂንካ ከተመሰረተችበት ከ60 ዓመታት ወዲህ ጀምሮ ባልታየ ድርቅ ከተማዋን በምዕራብና ምስራቅ የከበቡዋት የ‹አፊያ› እና ‹ኔሪ › ወንዞች ሙሉ በሙሉ በመድረቃቸው የከተማው እንስሳትም ለከፍተኛ የመኖና ውኃ እጥረት ተደርገውብናል ›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ የመጠጥ ውኃ እስከ 15 ቀናት እንደሚጠፋ፣ በሦስት ቀን አንድ ጊዜ ውሃ የሚያገኙ የታደሉ እንደሚባሉ፤ በከተማው በአስፈሪው አቧራና ፀሃይ የውሃ ጄሪካን ይዞ መዞር ለህጻናት፣ ወደ ሥራ መሄድና መምጣት ለቤተሰብ ፈታኝ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ ፡፡
“ጂንካ ወይናደጋ የአየር ጸባይ ያላት ሆና እንዲህ ያለው ፈተና ከገጠማት በቆላማው አካባቢ የሚደርሰውን ጉዳት ለመገመት ያስቸግራል” የሚሉት ነዋሪዎች በሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እንስሳት በማለቃቸው ከተማዋ በመጥፎ ጸረን መሞላቱዋን ይናገራሉ።
የከብት መኖና ውኃ እጥረት ከተዛማጅ ወረርሽኝ በሽታ ጋር እንስሳትን እየጨረሰ በመሆኑና የአርብቶ አደሩ የምግብ ምንጭ የእንስሳት ተዋጽኦ በመሆኑና ይህ ተዋጽኦ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ አረጋዊያንና ህጻናት በከፍተኛ ምግብ እጥረት ሳቢያ ለበሽታ ተዳርገዋል። አስቸኳይ ዕርዳታ ካልደረሰላቸው የአርብቶአደሮች ህይወት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ የግብርናና የጤና ባለሙያዎች ሥጋታቸውን እየገለጹ ነው ፡፡
በዞኑ የሚታየው ድርቅ ወደ ደጋው አካባቢም ስለተዛመተ በከተማዋ የደጋ እህሎች የሚባሉት አተር፣ ባቄላ፣ ስንዴ ፣ገብስ ፣ጠመጅ፣ ወዘተ ዋጋቸው ንሯል፡፡ 5ኪሎ በሚይዘው መስፈሪያ የሽሮ አተር በ150 ብር እየተሸጠ ሲሆን፡ ጤፍ በኩንታል 2000 (ሁለት ሺ ) ከነበረበት በሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ 2300 ብር ገብቷል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች የማንጎ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ለህጻናትና ቤተሰብ የምግብ ድጋፍ ባይሆን ኖሮ እስካሁን ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ይከሰት ነበር ይላሉ፡፡
አስተያየት ሰጪዎች ‹‹ የመንግስት ባለሥልጣናት ልጆቻቸውን የታሸገ ውኃ ያጠጣሉ፣ የምግብ እህሎችን ከፈለጉበት ቦታ ያስመጣሉ፣ችግሩ ስለማይደርሳባቸው መጠኑንና አሳሳቢነቱን አልተረዱትም፡፡ በዚህ አሳሳቢ ጉዳይ ላይ ነዋሪውን ሰብስበው አላወያዩም ፡፡ ምን እየተደረገ እንደሆነ አልገለጹለትም፣ ከሥጋቱ አልታደጉትም፡፡ የዞኑ ህዝብ በተለይም አርብቶአደሩ በዚህ ዓይነቱ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የድረሱልን ጥሪ እያሰማ ባለበት፣ ይህንን ለሚመለከታቸው ክፍሎች ማሳወቅና አፋጣኝ መፍትሄና ዕርዳታ መፈለግ ሲገባቸው እነርሱ ‹‹ የአርብቶአደር ሲምፖዚየም ›› በሚል አርብቶአደሩን ዞን ከተማ ጠርተው ያስጨፍራሉ፡፡ “ ሲሉ ተችተዋል።