ኢሳት (ጥር 8፥ 2009)
ኢትዮጵያ በአለም ካሉ ሃገራት መካከል የግል የቤት ተሽከርካሪ ባለቤትነት በጣም አነስተኛ ሆኖ የተመዘገበባት ሃገር መሆኑናን ቢቢሲ ሰኞ ዘገበ።
ሃገሪቱ ላለፉት በርካታ አመታት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳስመዘገበች ቢነገርላትም፣ የሁለት ተሽከርካሪዎች ድርሻ በአማካይ ለአንድ ሺ ሰዎች ሆኖ መገኘቱን የዜና አውታሩ ዴሎይት የተሰኘ ኩባንያ ጥናት ዋቢ በማድረግ ለንባብ አብቅቷል።
የግል የቤት ተሽከርካሪዎች እንደቅንጦት በሚታይባት ኢትዮጵያ ዕድሜ ጠገብ የሆኑ ተሽከርካሪዎች እንኳን ወደ ወደ ሃገሪቱ ሲገቡ እስከ 300 ፐርሰንት ታክስ እንደሚከፈልባቸው ቢቢሲ ዘግቧል።
በቤት ተሽከርካሪ ንግድ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው ሄኖክ ደምሰው ወደ ሃገሪቱ ለንግድ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ከጅቡቲ ወደብ ወደ መሃል ሃገር እስኪጓጓዙ ድረስ ታክስን ጨምሮ የተለያዩ ክፍያዎች የሚፈጸምባቸው በመሆኑ ዋጋው ውድ ሊሆን መቻሉን አስረድቷል።
በጎረቤት ኬንያ በስምንት ሺ ዶላር አካባቢ የሚሸጡ ያገለገሉ የቤት ተሽከርካሪዎች የ100 ፐርሰንት ጭማሪ ታይቶባቸው እስከ 16ሺ ዶላር እንደሚሸጡ ቢቢሲ በማነጻጸሪያነት አቅርቧል።
በመዲናይቱ አዲስ አበባ ከተመሰረቱ 25 አመት ያለፈባቸው ተሽከርካሪዎች በትንሹ 15ሺ ዶላር (ከ300ሺ ብር) በላይ እንደሚጠየቅባቸው የዜና አውታሩ በዘገባው አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በበኩሉ ወደ ሃገሪቱ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች አምስት የተለያዩ የግብር ክፍያዎች ተግባራዊ እንደሚደረግባቸው ገልጿል።
በሃገሪቱ ያለውን የተሽከርካሪ ውድነት ለመቅረፍ የመገጣጠሚያ ፋብሪካዎች ቢቋቋሙ የመሸጫ ዋጋቸው እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር እንደሚደርስና ዋጋው ለአብዛኛው ነዋሪ የማይቀመስ መሆኑም ተመልክቷል። በሃገሪቱ ውስጥ የሚመረቱት ተሽከርካሪዎች ከዋጋቸው መወደድ በተጨማሪ በተጠቃሚው ዘንድ ያላቸው ተፈላጊነት አነስተኛ መሆኑንም የተለያዩ ተጠቃውሚዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ወደ 100 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ባላት ኢትዮጵያ እስካለፈው አመት ድረስ ወደ 700ሺ አካባቢ የሚደርሱ ተሽከርካሪዎች ብቻ መኖራቸውን የትራንስፖርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የቻይና ኩባንያዎች ጨምሮ የኤፈርት ንብረት የሆኑ ድርጅቶች በአመት እስከ 8ሺ የሚደርሱ ተሽከርካሪዎች በሃገር ውስጥ በማምረትና በመገጣጠም ለተጠቃሚው እንደሚያቀርቡም ለመረዳት ተችሏል። በዘርፉ ተሰማርተው የነበሩ የግል ድርጅቶች በመንግስት ይደርስብናል ያሉትን ጫና በመቃወም ከስራቸው መውጣቱ ይታወሳል።