ኢሳት (ጥር 5 ፥ 2009)
አሜሪካ ከ20 አመት በፊት በሱዳን ላይ የጣለቸውን የኢኮኖሚ ማዕቀብ አርብ በይፋ እንደምታነሳ የአሜሪካ ባለስልጣናት ይፋ ማድረጋቸው ተገለጸ።
አሜሪካ ሃገሪቱ ሽብርተኝነትን ትደግፋለች በሚል በሱዳን መንግስት ላይ ከ20 አመት በፊት የንግድና የፋይናስ ማዕቀብን ጥላ የነበረ ሲሆን፣ ሃገሪቱ ሽብርተኛነትን ለመዋጋት ተጨባጭ ጥረት በማድረጓ እገዳው ሊነሳላት መቻሉን ቢቢሲ ዘግቧል።
ተሰናባቹ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በቀጣዩ ሳምንት ስልጣናቸውን ለተመራጩ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከማስረከባቸው በፊት ከሱዳን ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል ፋላጎት ማሳየታቸው ተመልክቷል።
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ከሱዳኑ አቻቸው ጋር ሁለቴ ተገናኝተው በማዕቀቡ ዙሪያ ምክክርን ሲያካሄዱ የነበረ ሲሆን፣ በሱዳን የአሜሪካ ልዩ መልዕከተኛ የሆኑት አምሳደር ዶናልድ ቡዝ ወደ ካርቱም በርካታ ጊዜ መመለሳቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ (AFP) አርብ ዘግቧል።
አሜሪካ በሱዳን መንግስት ላይ የጣለችውን የኢኮኖሚ ማዕቀብ ብታነሳም ሃገሪቱ በመንግስት ደረጃ ለሽብርተኛ ድጋፍ ታደርጋለች ተብሎ የሰፈረው የጥቁር መዝገብ ግን ቀጣይ እንደሚሆነ ታውቋል።
አሜሪካ ከበርካታ አመታት ፍለጋ በኋላ ከጥቂት አመታት በፊት መግደል የቻለችው የአልቃይዳው መሪ ኦሳማ ቢን-ላደን እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1992 አም እስከ 1996 አም ድረስ በሱዳን ቆይታ እንደነበራቸው የሚታወስ ነው።
ድርጊቱን ተከትሎ የአሜሪካ መንግስት የደቡብ ሱዳን መንግስት እስላማዊ ታጣቂዎችን ትደግፋለች በማለት በሃገሪቱ ላይ ማዕቀብ ጥላ ቆይታለች።
የሱዳኑ ፕሬዚደንት ኦማር አልበሽር በአለም አቀፉ የጦር ፍርድ ቤት የተጣለባቸውን የእስር ትዕዛዝ ምክንያት በማድረግ አሜሪካ ፕሬዚደንቱ ለተባበሩት መንግስታት የመሪዎች ጉባኤ መምጣት በፈለጉ ጊዜ የመግቢያ ቪዛን መከልከሏም ይታወቃል።
በሱዳን የዳርፉር ግዛት ለበርካታ አመታት በቆየው ግጭት የሱዳኑ ፕሬዚደንት የጦር ወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል ተብለው የእስር ትዕዛዝ እንደተላለፈባቸው አይዘነጋም።
ኦማር አልበሽር ይህንኑ የእስር ትዕዛዝ ለመሸሽ ሲሉ የአለም አቀፍ የጦር ፍርድ ቤት አባል ሃገራት ከመጓዝ ቢቆጠቡም፣ ከአንድ አመት በፊት አባል ሃገር ወደሆነችው ደቡብ አፍሪካ ያደረጉት ጉዞ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።
ደቡብ አፍሪካ ለፕሬዚደንቱ ያለመከሰስ ልዩ መብት በመጣስ ፕሬዚደንት አልበሽር ወደ ሃገሪቱ እንዲገቡ መፍቀዷ በደቡብ አፍሪካ የፖለቲካ የፖለቲካ ልዩነት መፍጠሩም የሚታወስ ነው።