ኢሳት (ጥር 5 ፥ 2009)
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ያሉ ሃገራት በአለም የንግድ እንቅስቃሴ መዋዠቅ ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ዕድገታቸው ፈታኝ እንደሚሆን የአለም ባንክ አስታወቀ።
የፈንረጆቹ 2017 አም አዲስ አመት የአለም ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን አስመልክቶ ሪፖርትን ያወጣው ባንኩ በተያዘው አመት ከሰሃራ በታች ያሉ ሃገራት የኢኮኖሚ ዕድገት በአማካኝ 2.9 በመቶ አካባቢ ሊያድግ እንደሚችል ይፋ አድርጓል።
ኢትዮጵያ በዚሁ አመት ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷ በሁለት አህዝ እንደሚያድግ ብትገልጽም የአለም ባንክ ዕድገቱ በስምንት በመቶ አካባቢ እንደሚሆን ትንበያውን አስቀምጧል።
የኢትዮጵያ ውጭ ንግድ መዋዠቅ በሃገሪቱ የቆየው የፖለቲካ ውጥረት፣ እንዲሁም የፋይናንስ ውጭ ምንዛሪ ክምችት እጥረት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ማነቆ ሆነው መገኘታቸውን ከባንኩ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።
የኢትዮጵያ ዋነኛ የልማት አጋር የሆነው አለም ባንክ እነዚህንና ተጓዳኝ ችግሮች በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ አስታውቋል።
የጎረቤት ኬንያ እና የዩጋንዳ ኢኮኖሚ ዕድገት በተያዘው በጀት አመት በሰባት በመቶ አካባቢ ያድጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የአለም የንግድ እንቅስቃሴ መዋዠቅ በተለይ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሃገራት ዘንድ ተፅዕኖው ከፍተኛ እንደሚሆን ባንኩ በሪፖርቱ አስፍሯል።
ይሁንና የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ከተቀሩ ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ጋር ሲነጻጸር ኢኮኖሚያዊ ዕድገታቸው በተሻለ ሁኔታ ላይ እንደሚቀጥል የተተነበየ ሲሆን፣ የአለም የኢኮኖሚ ዕድገትም በአማካይ በ2.7 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሁኔታ ዙሪያ መግለጫን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ሃገሪቱ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ ወዳጅ የተባሉ ሃገራት ገንዘባቸውን በኢትዮጵያ እንዲያስቀምጡ በመደረግ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃገሪቱን ስምና ተቀምጧል ያሉትን የገንዘብ መጠን ከመግለጽ የተቆጠቡ ሲሆን፣ መንግስት ሃገሪቱ ያጋጠማትን የፋይናንስ ችግር ለማገዝ ከ27 ቢሊዮን ብር በላይ የመንግስት ቦንድ እንዲዘጋጅ ወስኗል።
ይኸው ውሳኔ በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የሚጸድቅ ሲሆን፣ የአዋጁ መውጣትን ተከትሎም አበዳሪ አካላት ገንዘብ ለመንግስት ማበደር እንደሚጀምሩ ይጠበቃል። ብድሩ የአምስት አመት የእፎይታ ጊዜ ታክሎበት በ10 አመት ውስጥ የሚከፈል እንደሚሆን መንግስት ገልጿል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በበኩላቸው መንግስት ያጋጠመውን የፋይናንስ እጥረት ለመፍታት እየወሰደ ያለው ዕርምጃ የሃገሪቱን የዋጋ ግሽበት ከፍ እንዲል ከማድረግ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ሊያመጣ እንደሚችል አስረድተዋል።
የብር የመግዛት አቅም መቀነስን ተከትሎ የፌዴራል እና የክልል መንግስታት የተጨማሪ በጀት ጥያቄን እያቀረቡ እንደሆነም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ ያመልክታል።