ጥር ፪ (ሁለት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኢትዮጵያ ውስጥ ህዝባዊ አመጽ ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ በአገዛዙ ተስፋ በመቁረጥ ሃብታቸውን የሚያሸሹ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮአል።
ስማቻው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የባንክ ባለሙያ እንደገጸሉት፣ ባለፉት 4 ወራት በርካታ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ገንዘባቸውን እያወጡ ጥገኝነት ወደ ሰጣቸው አገር ሲመለሱ፣ ሌሎች ደግሞ ወደ ጎረቤት አገራት በመሄድ በንግድ እንቅስቃሴ ለመሳተፍ እየሞከሩ ነው፡። ለኢትዮጵያውያኑ መልቀቅ ምክንያቱ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት መጨመር ቢሆንም፣ የዘመዶቻቸው ግፊትም ተጽእኖ እንዳለበት አክለዋል። ገንዘባቸውን ያወጡ ትውለደ ኢትዮጵያውያን ለምን እንደሚመለሱ ሲጠየቁ፣ በአገሪቱ ከታየው አመጽ ጋር በተያያዘ የተወሰደው እርምጃ ተስፋ የሚሰጥ ሆነው እንዳላገኙት፣ ንብረታቸው ቢወድም በቂ ዋስትና እናገኛለን ብለው ባለማመን፣ እንዲሁም ዘመዶቻቸው ከደህንነታቸው ጋር በተያያዘ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የሚያደርጉትን ግፊት በዋናነት ጠቅሰዋል። በአገሪቱ የሚታየው ቢሮክራሲና ሙስና እንዲሁም ሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች በአንድ ብሄር ተወላጆች ቁጥጥር ስር መግባቱንም በምክንያትነት ያቀርባሉ።
ወደ አገሪቱ የሚገባው የውጭ ኢንቨስትመንትም በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን የሚናገሩት እነዚህ ምንጮች፣ መንግስት የውጭ ምንዛሬ ገቢውን ተፍስ አድረጎ የሚጠባበቀው ከዲያስፖራው ነው ብሎአል። አገዛዙ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲል ከህዝባዊ አመጹ ጋር በተያያዘ ምንም ችግር አልጠፈጠረም ቢልም፣ እውነታው ግን በግልጽ የሚታይ ነው ብሎአል። ዶላር ለማግኘት ጭንቅ እየሆነ መምጣቱን የሚናገረው ባለሙያው፣ በዚህም የተነሳ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ እቃዎች እየቀነሱና የዋጋ ንረቱን ቀስ በቀስ እያሳደጉት ነው ሲል አክሏል።
አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከቱሪዝምና ከአንዳንድ አገልግሎቶች የሚገኘውን ገቢ ከማወክ በስተቀር በኢኮኖሚው ላይ ያመጣው ተጽእኖ የለም በማለት ተናግረዋል። ይሁን እንጅ የተለያዩ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ሳይቀሩ ከህዝባዊ አመጹ በሁዋላ በኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት መቀነሱን እየጻፉ ነው።