ሱዳንን መሸጋገሪያ በማድረግ ከኢትዮጵያ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ

ኢሳት (ጥር 1 ፥ 2009)

የሱዳን ባለስልጣናት ሃገሪቱ መሸጋገሪያ በማድረግ ከኢትዮጵያ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ስጋት እንዳሳደረባቸው ገለጹ።

የስደተኞች ዝውውርን ለመቆጣጠር የተቋቋመው የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ አገልግሎት ሃላፊ የሆኑት መሃመድ ሃምዳን ባለፉት ሰባት ወራቶች ብቻ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን የሆኑ 1ሺ 500 ስደተኞች በቁጥጥር ስር ሊውሉ መቻላቸውን ለሱዳን መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

ከኢትዮጵያ የሚሰደዱ ሰዎች ሱዳንን ለመሸጋገሪያነት በመጠቀም ወደ ግብፅ፣ ሊቢያ እና አውሮፓ ሃገራት ለመግባት ጥረት እንደሚያደርጉ ሃላፊው አስረድተዋል።

ትላንት እሁድ ብቻ 115 ስደተኞች በሰሜን ሱዳን ድንበር አካባቢ በልዩ የጸጥታ ሃይሎች ለእስር መዳረጋቸውን ያወሱት መሃመድ ሃምዳን የህገወጥ ስደተኞቹ ጉዳይ ለሱዳን አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ለሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ ገልጸዋል።

በድንበር ጠባቂ ልዩ ሃይሎች የተያዙት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ለሱዳን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ተላልፈው ከተሰጡ በኋላ ህጋዊ ውሳኔን እንደሚያገኙ ጋዜጣው በዘገባው አስፍሯል።

ከዚሁም ቀደም ሱዳን መሸጋገሪያ አድርገው ወደተለያዩ ሃገራት ለመሰደድ ሙከራ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ለኢትዮጵያ ተላልፈው መሰጠታቸው ይታወሳል።

በቅርቡ ከአውሮፓ ህብረት ልዩ የገንዘብ ድጋፍን ያገኘችው ሱዳን በድንበሯ ዙሪያ ቁጥጥሯን በማጠናከር የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እንዲሁም የሶማሌ ስደተኞችን በመያዝ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ማድረጓንም ለመረዳት ተችሏል።

ባለፈው አመት በኢትዮጵያ በተለይ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ከሃገሪቱ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በቅርቡ ሪፖርቱን ያወጣው የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት (IOM) ባለፈው የፈረንጆች አመት ጦርነት ዕልባት ወዳላገኘባት የመን ብቻ ወደ 90 ሺ ኢትዮጵያውያን መሰደዳቸውን ይፋ እንዳደረገ መዘገባችን ይታወሳል።

ከየመን በተጨማሪ ቁጥራቸው ያልታወቀ ስደተኞችም በኬንያ እንዲሁም በተለያዩ የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት የተሰደዱ ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩት በማላዊ እና ታንዛኒያ እስር ቤቶች እንደሚገኙ ታውቋል።

የጎረቤት ሱዳን ባለስልጣናት በበኩላቸው ወደ ሃገሪቱ በመግባት ወደ ተለያዩ ሃገራት ለመሰደድ ጥረት እያደረጉ ያሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ስቃዮች እየደረሱባቸው እንደሚገኝ ይገልጻሉ።

የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት ከየመን መውጫን አጥተው የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በተለያዩ መንገዶች ለማጓጓዝ ጥረት እያደረገ መሆኑንም አስታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የዚምባብዌ የጸጥታ ሃይሎች ወደ ሃገሪቱ በህገወጥ መገንድ ገብተዋል የተባሉ 34 ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል።

በሳምንቱ መገባደጃ ከተያዙት ኢትዮጵያውያን መካከል ሁለቱ የ11 እና የ12 አመት ታዳጊ ህጻናት ሲሆኑ ስደተኞቹ ከዚምባቡዌ መዲና ሃራሬ 72 ኪሎሜርት ርቀት ላይ በምትገኘው የማሮንዴራ ከተማ ሊያዙ መቻላቸውን ኒውስ ዴይ የተሰኘ የሃገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል።

ኢትዮጵያውያኑ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ፍርድ ቤት ቢቀርቡም በእንግሊዝኛው ቋንቋ መግባባት ባለመቻላቸው ከ10 ቀን በኋላ በተለዋጭ ቀጠሮ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ መሰጠቱ ታውቋል።

በሃራሬ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለስደተኞቹ አስተርጓሚን እንዲመደብ ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ማስተላለፉን ጋዜጣው በዘገባው አስነብቧል።