የብሪታኒያ መንግስት ለትምህርታዊ ፕሮግራሞች ሊሰጥ የነበረውን ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ አገደ

 

ኢሳት (ጥር 1 ፥ 2009)

የብሪታኒያ መንግስት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት ለሚተላለፉ ትምህርታዊ ፕሮግራሞች ሊሰጥ የነበረውን ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ አገደ።

የሃገሪቱ አለም አቀፍ የልማት ትብብር ባለፈው ወር “የእኛ” የሚል መጠሪያ ላላቸው ቡድኖች የ5.2 ሚሊዮን ፓውንድ (ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ) ድጋፍ ለማድረግ ውሳኔን አስተላልፎ እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል።

ይሁንና፣ ድርጅቱ ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የብሪታኒያ የፓርላማ አባላት እንዲሁም የመገናኛ ተቋማት ገንዘቡ ከታለመለት አላማ ውጭ ሊውል ይችላል ሲሉ ተቃውሞን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

ተቃውሞውንም ተከትሎ የሃገሪቱ አለም አቀፍ የልማት ትብብር ለኢትዮጵያ ሊሰጥ የነበረው ድጋፍ እንዲያዝና በቀረቡ ቅሬታዎች ዙሪያ ምርመራ እንዲካሄድበት ትዕዛዝ አስተላልፎ እንደነበር ይታወሳል።

ለኢትዮጵያ ሊሰጥ በታሰበው የገንዘብ ድጋፍ ዙሪያ የተካሄደውን ምርመራ ተከትሎ ውሳኔውን ያስታወቀው የብሪታኒያ መንግስት የገንዘብ ስጦታው ሙሉ ለሙሉ እንዲቆም መደረጉን ይፋ አድርጓል።

የብሪታኒያው አለም አቀፍ የልማት ትብብር “የኛ”  በሚል ስም ለሚጠሩት አካላት የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የቡድኑ አባላት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ለማህበረሰቡ ትምህርታዊ ግንዛቤዎችን የሚሰጡ ፕሮግራሞች እንዲተላለፉ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል።

አምስት አባላት ያቀፈው ይኸው ቡድን በሙዚቃ፣ በድራም፣ እንዲሁም በሙዚቃዎች በአስገድዶ መደፈር፣ በሴቶች መብት እና ያለዕድሜ ጋብቻ ዙሪያ የተለያዩ የኪነጥበብ ስራዎችን ሲያቀርብ መቆየቱ የሚታወቅ ነው።

የብሪታኒያው አለም አቀፍ የልማት ትብብር ባለፉት አምስት አመታት በዚሁ ቡድን የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ ቢቆይም፣ የሃገሪቱ የፓርላማ አባላት፣ የመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ድጋፍ ከታለመለት አላማ ውጭ ሊውል ይችላል ሲሉ ተቃውሞን ማቅረብ ጀምረዋል።

የገንዘብ ድጋፉ መቋረጡን ያስታወቀው አለም አቀፍ የትብብር ድርጅቱ የታክስ ከፋይ ገንዘብን በተሻለ ሁኔታ ጥቅም ላይ ለማዋል አማራጮች በመታየታቸው “የእኛ” በሚል መጠሪያ ካላቸው አካላት ጋር የነበረው ትብብር እንዲቋረጥ ተወስኗል ሲል በመግለጫው ማመልከቱን ዴይሊ ሜይል ጋዜጣ ዘግቧል።

የብሪታኒያ መንግስት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት ተመሳሳይ ፕሮግራሞችን በመደገፍ ላይ ሲሆኑ፣ የሌሎች ሃገራት ድጋፍ በዚህ ውሳኔ አለመካተቱ ታውቋል።