ታኅሣሥ ፳፰ (ሃያ ስምንት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በምስራቅ አፍሪካ የሚታየውን የዝናብ እጥረት ተከትሎ ዳግም የከፋ የርሃብ አደጋ ማንዣበቡን የአየር ንብረት ትንበያ ባለሙያዎች አስታወቁ። በድርቁ ምክንያት በተለይ አርብቶ አደር አካባቢዎች ክፉኛ ተጠቂ ሆነዋል። የምግብ እጥረት፣ የሰብል መበላሸት እና የእንስሳት መጎዳት በአርብቶ አደሮች ሕይወት ላይ ከፍተኛ አደጋ ደቅኗል።
በኡጋንዳ፣ ኬኒያ፣ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ 12 ሚሊዮን ዜጎች ለከፋ ድርቅ ተጋልጠዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም የምግብ እና ግብርና ተቋም FAO ኃላፊ የሆኑት ሽኩሪ አህመድ እንዳሉት ”በኢሊኖ ምክንያት በቀጠናው ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል። በአሁኑ ወቅት ያለው የርሃብ አደጋ ወደ ከፋ ሁኔታ ሊቀየር ይችላል የሚል ስጋቱ አለን” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በኢትዮጵያ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች አፋጣኝ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። በርሃቡ ምክንያት በድርቅ ተጠቂ የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ማኅበራዊ ህይወታቸው ተቃውሷል። ለከብቶቻቸው ግጦሽ ፍለጋ መኖሪያ ቀያቸውን በመልቀቅ ተሰደዋል።ታዳጊዎች ትምህርታቸውን በማቋረጣቸው ምክንያት ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል።
የጉጂ ዞን የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ነጋሽ ኡላላ ”በዞኑ በደረሰው የርሃብ አደጋ ምክንያት ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመተው አካባቢውን ለቀው በመሄዳቸው ምክንያት ሁለትትምህርት ቤቶችን ለመዝጋት ተገደናል። በዚህ አካባቢ የሚኖሩ አርብቶ አደሮች ልጆቻቸውን ይዘው ግጦሽ እና ውሃ ፍለጋ ፈልሰዋል። እስካሁን ባለው መረጃ 186 ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ 52 ሽህ ተማሪዎች በድርቁ ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠዋል።’ አፋጣኝ በሆነ ሁኔታ ለተጎጂ ዜጎች እርዳታ ማድረስ ካልተቻለ ለቀጣይ በቀጠናው ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ ሊደርስ ይችላል ሲል ፋኦን ጠቅሶ DW ዘግቧል።