ኢሳት (ታህሳስ 28 ፥ 2009)
ነገ ቅዳሜ በመላው የክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረውን የገና በዓል አከባባር አስመልክቶ የሃይማኖት አባቶች መልዕክት አስተላለፉ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ህብረትና የኢትዮጵያ መካነ-እየሱስ ቤተክርስቲያን መሪዎች የእምነቱ ተከታዮች በአሉን ችግረኞችን በመደገፍ እንዲሁም በመከባበርና የታመሙ ሰዎችን በመጠየቅ አክብረው እንዲውሉ በመልዕክታቸው ጠይቀዋል።
የበአሉ አከባበር በተለይ በመዲናዋ አዲስ አበባ ከዋዜማው ጀመሮ በደማቅ ሃይማኖታዊ ሰነስርዓት በመከበር ላይ ሲሆን፣ በርካታ የዕምነቱ ተከታዮች ወደ ቤተክርስቲያኖች በማቅናት በሃይማኖታዊ ስነስርዓቶችን እየታደሙ እንደሆነ ከሃገሪ ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድን አስመልክቶ ለእምነቱ ተከታዮች መልዕክትን ያስተላለፉ የሃይምኖት መሪዎች (አባቶች) ዕለቱ ዘላቂ ሰላምና አንድነት ለማስፈን ትኩረት የሚሰጥበት በዓል እንዲሆን ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ይኸው የዘንድሮው የገና በዓል ነዋሪነታቸው በዚህ በአሜሪካ እና በተለያዩ የአለማችን ሃገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶች በመከበር ላይ እንደሆነም ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በአለማችን ከ300 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የገናን በዓል ነገ ቅዳሜ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነስርዓቶች እንደሚያከብሩም ኒውስ ፕሬስ የተሰኘ ጋዜጣ አርብ ዘግቧል።
ሩሲያ፣ ግሪክና በአውሮፓ የሚገኙ የዕምነቱ ተከታዮች ዕለቱን ከዋዜማው ጀምሮ በደማቅ ስነስርዓት በማክበር ላይ ሲሆኑ፣ በግብፅ የሚገኙ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችም የገናን በዓል በተመሳሳይ ሁኔታ እያከበሩ እንደሚገኙ ተመልክቷል።
የአውሮፓ የዘመን አቆጣጠርን የሚከተሉ በርካታ የአለማችን ሃገራት ከአንድ ሳምንት በፊት የገናን በዓል ማክበራቸው ይታወሳል።