በኦሮሚያ በተባረሩት አመራሮች ቦታ የሚሾም እየጠፋ ነው። የክልሉ ፕ/ት ከህወሃት ጋር የሚያጋጫቸውን ንግግር ተናግረዋል።

 

ታኅሣሥ ፳፯ (ሃያ ሰባት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ኦህዴድ በቅርቡ በተለያዩ የአመራር ደረጃ ላይ ከሚገኙ ባለስልጣኖች ጋር ግምገማ አካሂዷል። ግምገማው የህወሃትን የበላይነት ይቃወማሉ የተባሉ የተለያዩ አመራሮችን ለማባረር የታቀደ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎም በርካታ አመራሮች ከሃላፊነት ተነስተው ደሞዝ ብቻ እየተከፈላቸው ተንሳፈው ይገኛሉ። ለእስር እንዳረጋለን ብለው የፈሩት ደግሞ እየኮበለሉ ወደ ተለያዩ አገራት እየተሰደዱ ነው።

ኦህዴድ በስልጣን ባነሳቸው አመራሮች ቦታ አዳዲስ አባላቱን ለመሾም ቢሞክርም፣ በቂ ሰው አላገኘም። ብዙዎቹ ከድርጅቱ ጋር በጋራ የመስራት ፍላጎት የላቸውም። አንዳንድ ተሻሚዎች በስልጣን ከተባበሩት ቢብሱ እንጅ የተሻሉ አለመሆናቸውን ምንጮች ይገልጻሉ።

ኦህዴድ ውስጥ ህወሃትን በሚደግፉና በሚቃወሙ አመራሮች መካከል ግልጽ መከፋፋል ተፈጥሯል። በቅርቡ በአመራርነት የተሾሙት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ የህወሃት ታማኝ ሰው ከሚባሉት ከአቶ በክረ ሻሌ ወይም በቅጽል ስማቸው ገብረመድህን ሻሌ እንዲሁም ከሌሎች የህወሃት ባለስልጣናት ጋር ግጭት ውስጥ የሚያስገባቸውን ንግግር ለስራ አስፈጻሚ አባላት ተናግረዋል። አቶ ለማ በስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ “ከእንግዲህ ወዲህ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ቦታዎችን ለማንኛው የህወሃት አባልም ይሁን የህወሃት አባል ነኝ እያለ ለሚመጣ ግለሰብ እንዳትሰጡ፣ እስከዛሬ የሰጣችሁት ትክክል አልነበረም፣ ከዚህ በሁዋላም ማንኛውም ባለስልጣን ቢያዛችሁ እኔም ጨምሮ መሬት እንዳትሰጡ “ ብለው መናገራቸው ሌሎችን አባላት ማስደንገጡን ምንጮች ገልጸዋል።

አቶ ለማ እንዲህ አይነት ንግግር ለመናገር ለምን እንደፈለጉ ግልጽ ባይሆንም፣ በአንድ በኩል ግለሰቡ ራሳቸውን ተቃዋሚ አድርገው በማቅረብ፣ ጸረ ህወሃት አቋም ያላቸውን ሰዎች ለመለዬት ካልሆነም በኢህአዴግ ውስጥ እየታየ ያለው መፈረካካስ ስጋት ላይ ስለጣላቸው ከአሁኑ ከህዝብ ጋር ለመታረቅ ሊሆን ይችላል ሲሉ ምንጮች አስተያየታቸውን ይገልጻሉ።

አቶ ለማ ከ10 ቀናት በፊት ድሬዳዋን በጎበኙበት ወቅት “የሶማሊ ክልል ልዩ ሃይል ወደ ኦሮምያ እየገባ የቀንድ እና የጋማ እንስሶችን እየዘረፈ መሆኑን “ ህዝቡ አቤቱታ ያቀረበላቸው ሲሆን፣ እሳቸውም “ በሚቀጥሉት 5 አመታት ውስጥ ድንበሩ እንዲሰመር ማድረግ የመጀመሪያው ስራዬ ይሆናል፣ ድንበሩ ከተሰመረ በሁዋላ አንድ የሶማሊ ልዩ ሃይል ፍየል እንኳን ቢነካ የአጸፋ እርምጃ እንወስድበታለን” በማለት ተናግረዋል።

ኢህአዴግን በመሰረቱት አራቱ ድርጅቶች መካከል ያለው አለመግባባት እየሰፋ መምጣቱንም መረጃዎች ያመለክታሉ። በአስቸኳይ አዋጁ ሰበብ ህወሃት በተቆጣጠረው ወታደራዊ ሃይል ክልሎችን ስልጣን አልባ እያደረገ ነው በሚል በብአዴንና ኦህዴድ ውስጥ ቅሬታዎች እየበዙ ነው። በርካታ የብአዴን አመራሮች ከስልጣን ውጭ የተደረጉ ሲሆን፣ ክልሉን በበላይነት የሚያስተዳድረው ወታደራዊ እዙ ነው። የክልሉ ፕ/ት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ይህ ነው የሚባል የመወሰን ስልጣን የሌላቸው ሲሆን፣ አገሪቱ የተረጋጋች በሚመስልበት ወቅት ከስልጣን ለማንሳት እቅድ መኖሩን በአንድ የህወሃት ስብሰባ ላይ መገለጹን ምንጮች ገልጸዋል።

ኦህዴድም ክልሉን ሙሉ በሙሉ ለህወሃት ወታደራዊ አመራሮች ካስረከበ በሁዋላ፣ ድርጅቱን ጥለው የሚጠፉ እንዲሁም በውስጥ ሆነው የሚቃወሙ አባላት እየተበራከቱ ነው።