ኢሳት (ታህሳስ 27 ፥ 2009)
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰዋል ተብለው በእስር ላይ የሚገኙት ዶ/ር መረራ ጉዲና ሃሙስ ለምስክርነት ይቀርባሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ፍ/ቤት አለመቅረባቸው ታወቀ።
የሽብርተኛ ወንጀል ክስ ተመስርቶበት የሚገኘው የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ ቃል አቀባይና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ዮናታን ተስፋዬ ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ አቶ በቀለ ገርባ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና ሌሎች አካላት ለመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡለት መጠየቁን ለመረዳት ተችሏል።
ፍርድ ቤቱ ሃሙስ የመከላከያ ምስክሮቹን ማድመጥ በጀመረ ጊዜ በችሎት ይገኛሉ ተብለው የነበሩት ዶ/ር መረራ ጉዲና ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ሳይቀርቡ መቅረታቸውን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ፍርድ ቤቱም ዶ/ር መረራ ጉዲና በቀጣዩ ቀጠሮ ለችሎቱ እንዲቀርቡ ትዕዛዝን የሰጠ ሲሆን፣ አቶ በቀለ ገርባና ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ እንዲሁም ዶ/ር ያዕቆብ ሃይለማሪያም ለፍርድ ቤቱ የምስክርነት ቃላቸውን መስጠታቸውን አዲስ ስታንዳርድ መጽሄት አስነብቧል።
የሽብርተኛ ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው የሚገኙትና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ዋና ጸሃፊ የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተቃውሞን ሲያቀርቡ የነበሩት ዮናታን ተስፋዬ በማህበራዊ ድረገጽ ላይ ባቀረበው ጽሁፍ ሳይሆን የመንግስት ጭቆናና አፈና በመቃወም ነው ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ዮናታን የሚጽፋቸው የተለያዩ ጽሁፎችን ማንበባቸውን የተናገሩት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ በበኩላቸው ጹሁፎቹን በሽብርተኛ ወንጀል ክስ የሚያስከስሱ ናቸው ብለው እንዳማያምኑ አስረድተዋል።
ላለፉት ስምንት አመታት ከዮናታን በበለጠ ሁኔታ መንግስትን የሚተቹ ጽሁፎች እንድነበሩም ዶ/ር ዳኛቸው በምስክርነት ቃላቸው ለችሎቱ ገልጸዋል።
ሌላው የመከላከያ ምስክር ሆነው የቀረቡት ዶ/ር ያቆብ ሃይለማሪያም በበኩላቸው በማህበራዊ ድረገጾች ላይ በተጻፉ ጹሁፎች የሽብርተኛ ክስ ወንጀል እጅግ አሳሳቢ መሆኑንና ሰዎች ሃሳባቸው በነጻነት ለመግለጽ ሲሉ እነዚህን አማራጮች እንደሚጠቀሙ አስረድተዋል። ከሳሽ አቃቤ ህግ ተከሳሽ ለአመጽ የሚያነሳሱ ጽሁፎችን በማህበራዊ ድረገጾች ላይ አስፍሯል ሲል የሽብርተኛ ክስ መመስረቱ ይታወሳል።
ይሁንና ዮናታን ተስፋዬ በበኩሉ የቀረበበትን ክስ በማስተባባል በሽብርተኛ ወንጀልም ሆነ መንግስት በሃይል ለማስወገድ ተብለው በቀረቡ ጉዳዮች ዙሪያ አለመሰማራቱን አስረድቷል።
በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ስለተገደሉ ሰዎች መናገር ወንጀለኛ የሚያሰኝ ከሆነ ፍርዱን ከፈጣሪና ከታሪክ እንደሚያገኝ ለችሎት ገልጿል።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ዶ/ር መረራ ጉዲናና፣ ሌሎች የመከላከያ ምስክሮች ከ20 ቀን በኋላ የምስክርነት ቃላቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።