ኢሳት (ታህሳስ 27 ፥ 2009)
አለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (ሲ ፒ ጄ) በሁለት ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ላይ የተላለፈውን የእስር ቅጣት አወገዘ።
የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሽብርተኛ ወንጀል ተመስርቶባቸው የነበሩት ጋዜጠኞች ካሊድ መሃመድና ዳርሴማ ሶሪ ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል በማለት እያንዳንዳቸው በአምስትና በአራት አመት ከስድስት ወር የእስር ቅጣት እንዲቀጡ ፍርድ መስጠቱ ይታወሳል።
ይሁንና መቀመጫውን በዚሁ በአሜሪካ ያደረገው ኮሚቴ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስትስ (ሲፒጄ) በጋዜጠኞቹ ላይ የተላለፈውን ፍርድ የኢትዮጵያ መንግስት ሃሳብን በነጻነት ለመግለጽ በሚደረጉ ጥረቶች ላይ እያደረገ ያለውን ጭቆና የሚያሳይ ድርጊት ነው ሲሉ አስታውቀዋል።
የድርጅቱ የአፍሪካ ክፍል አስተባባሪ የሆኑት አንጀላ ኪንታል ሁለቱ ጋዜጠኞች ላይ የተጣለው የእስር ቅጣት ጋዜጠኞች ስራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ እና ፍርሃትን ለማሳደር የተወሰደ ዕርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።
ጋዜጠኞቹ ሽብርተኛ ባለመሆናቸው በአስቸኳይ መለቀቅ ይኖርባቸዋል ሲሉ ሃላፊዋ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የፌዴራሉ ከሳሽ አቃቤ ህግ ሁለቱ ጋዜጠኞች ሙያቸውን ከለላ በማድረግ የፅንፈኛ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብን ለማራመድና መንግስትን በሃይል ለመገልበጥ ከሌሎች አካላት ጋር ተንቀሳቅሰዋል ሲል ከአንድ አመት በፊት ክስ መመስረቱ ይታወሳል። ከሁለቱ ጋዜጠኞች ጋር 18 ግለሰቦች በተመሳሳይ ክስ ከአምስት አመት የሚበልጥ የእስር ቅጣት እንደተላለፈባቸው የሚታወቅ ነው።
ፍርድ ቤቱ ከቀናት በፊት የሰጠውን የፍርድ ውሳኔን ተከትሎ መግለጫን ያወጣው ሲፒጄ 16 ጋዜጠኞችን ለእስር ዳርጋ የምትገኘው ኢትዮጵያ በአለም ጋዜጠኞችን በማሰር የከፋ ተብለው ከተፈረጁ አምስት ሃገራት መካከል አንዷ መሆኗን አመልክቷል።
በተመሳሳይ ሁኔታ ባለፈው አመት ለእስር የተዳረገው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ለፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አቅርቦት የነበረው የዋስትና መብት በተያዘው ሳምንት ውድቅ እንደተደረገባት ታውቋል።
የነገረ-ኢትዮጵያ አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ጌታቸው በቁጥጥር ስር በዋለ ጊዜ የሽብርተኛ ወንጀል ክስ አቀርቦበት የነበረ ሲሆን ክሱ በቅርቡ “ማነሳሳት” በሚል መቀየሩ ታውቋል።
በጋዜጠኛው ላይ የቀረበው ይኸው ክስ በቀጣዩ ወር መታየት ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ሲፒጄ የክሱ ሂደት አሳስቦት እንደሚገኝ ገልጿል።