ኢሳት (ታህሳስ 26 ፥ 2009)
የአለም ጤና ድርጅት የበላይ ጠባቂ ቦርድ በተያዘው ወር ቀጣዩ የተቋሙ ሃላፊ ሆነው ለመመረጥ ከቀረቡ ተወዳዳሪዎች መካከል አምስቱን ለይቶ እንደሚያሳውቅ ገለጸ።
የቀድሞ የኢትዮጵያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖምን ጨምሮ የጣሊያን፣ የፈረንሳይ፣ የብሪታኒያ፣ የፓኪስታን፣ እና የሃንጋሪ ተወዳዳሪዎች በቦርዱ ምርጫ የሚካሄድባቸው መሆኑ ታውቋል።
ተወዳዳሪዎቹ በቅርቡ ስለድርጅቱ ያላቸው ራዕይ አስመልክቶ ያቀረቡትን ገለጻና የተደረገላቸውን ጥያቄ መሰረት በማድረግ አምስቱ ተወዳዳሪዎች በተያዘው ወር ተለይተው ለህዝብ ይፋ እንደሚደርጉ ይጠበቃል። በዚህም አንድ ሰው ከውድድር ውጭ ይሆናል።
በቅርቡ የሚሰባሰቡት የቦርዱ አባላት ለሚቀሩት አምስት ተፎካካሪዎች ቃለ-መጠይቆችን በቀጣይነት በማካሄድ የመጨረሻ ሶስት ተወዳዳሪዎችን ለአባል ሃገራት ድምጽ እንደሚያቀርቡ የጤና ድርጅቱ ይፋ አድርጓል።
የአለም ጤና ድርጅት የበላይ የቦርድ ጠባቂ ባለሙያዎችን ያካተተ 34 አባላት ያሉት ሲሆን፣ አባላቱ ለሶስት አመት የሚያገለግሉ እንደሆነ ድርጅቱ በድረ-ገጹ ካሰፈረው መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
በአሁሉ ወቅት ስድስት ተወዳዳሪዎች ቀርበው የሚገኙ ሲሆን፣ የቦርድ አባላቱ የተለያዩ መስፈርቶቹን በመገምገም ተወዳዳሪዎቹን የመለየት ስራ ያከናውናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
34ቱ የባለሙያዎች ቡድን ለይተው የሚያቀርቧቸው የመጨረሻዎቹ ሶስቱ ተወዳዳሪዎች በተያዘው አመት ግንቦት ወር የጤና ድርጅት አባል ሃገራት ድምፅ ይስጡባቸዋል።
አሸናፊ ሆኖ የሚለየው ተወዳዳሪም እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከሃምሌ 1, 2017 አም ጀምሮ የድርጅቱ የአመራር ቦታን የሚረከብ ሲሆን፣ በሃላፊነት ላይ ያሉት ዶ/ር ማርጋሬት ቻን ሁለተኛ የስልጣን ጊዜያቸውን ሰኔ 30 ያጠናቅቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የቦርዱ አባላት በሚሰጡት ድምፅ ከ10 በመቶ በታች ድምፅ የሚያገኝ ተወዳዳሪ ከተፎካካሪነት የሚሰናበት ሲሆን፣ ቦርዱ ሶስት እና ከዛም ያነሰ ተወዳዳሪን ለመጨረሻው ዙር የማቅረብ ስልጣን እንዳለው ለመረዳት ተችሏል።
ወቅታዊ ሙሉ የጤንነት ሁኔታን ጨምሮ ተወዳዳሪዎችን በጤና እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ብቃትና በቂ የስራ ልምድ እንዲኖራቸው በመስፈርትነት ተቀምጧል።