በብራዚል በእስር ቤት በተቀሰቀሰ ግጭት ከ50 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ

ኢሳት (ታህሳስ 25 ፥ 2009)

በብራዚል በሚገኝ አንድ እስር ቤት በተቀሰቀሰ የእስረኞች የእርስ በዕርስ ግጭት በትንሹ 56 ሰዎች መሞታቸውን የሃገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ።

አማዞናስ ተብሎ በሚጠራው የብራዚል ሰሜናዊ ግዛት ስር በሚገኝ አንድ እስር ቤት በተነሳው በዚሁ ግጭት ቁጥራቸው ይፋ ያልተደረገ እስረኞች ማምለጣቸውንም ቢቢሲ የእስር ቤቱን ሃላፊዎች ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

ለበርካታ ሰዓታት የቆየው ይኸው የእስረኞች ግጭት በሁለት ቡድን በተከፈሉ እስረኞች የተቀሰቀሰ ሲሆን፣ ድርጊቱ በ23 አመት የሃገሪቱ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛው እንደሆነም ተነግሮለታል።

የብራዚል ፖሊስ ከእስር ቤቱ ያመለጡ ሰዎችን ለመያዝ ጥረት በማድረግ ላይ ሲሆን፣ 30 እስረኞች በዘመቻው ሊያዙ መቻላቸውን የሃገሪቱ ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

592 እስረኞን የመያዝ አቅም ባለው እስር ቤት 1ሺ 244 ሰዎች በተጨናነቀ ሁኔታ ለእስር ተዳርገው የነበረው ሲሆን፣ በእስር ቤቱ የአደንዛዥ እፅን ጨምሮ ሌሎች ህገወጥ ድርጊቶች ይፈጸሙ እንደነበር ተመልክቷል።

ግጭቱ በተቀሰቀሰ ጊዜ 12 የሚሆኑ የእስር ቤቱ ጠባቂዎች ታግደው የነበረ ቢሆንም የጸጥታ አባላቱ ያለምንም ጉዳት መለቀቃቸውን የጸጥታ ሃላፊ የሆኑትን ስርጊዬ ፎንቴስ ገልጸዋል።

በእስር ቤቱ የጸጥታ አባላትና በእስረኞቹ መካከል የተካሄደን ድርድር ተከትሎ እሁድ የተቀሰቀሰው ፀብ ሰኞ ዕልባት ያገኘ ሲሆን፣ ከእስር ቤቱ ያመለጡ ግለሰቦችን ለመያዝ ግን ሃገር አቀፍ ዘመቻ በመካሄድ ላይ መሆኑ ታውቋል።

እንደፈረጆቹ አቆጣጠር በ1992 ዓም በመዲናይቱ ሳኦ ፖሎ በሚገኝ አንድ እስር ቤት ተቀሰቅሶ በነበረ ተመሳሳይ ግጭት 111 እስረኞች በጸጥታ ሃይሎች ተገድለው እንደነበር ቢቢሲ በዘገባው አውስቷል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ሰኞ ማናኡስ ተብሎ በሚጠራ ግዛት ስር በሚገኙ ሁሉት እስር ቤቶች በተቀሰቀሰ አመፅ 87 እስረኞች ከአንደኛው እስር ቤት ማምለጣቸውን የብራዚል ባለስልጣናት ይፋ አድርገዋል።

በእስር ቤቱ በተካሄደ ፍተሻ በርካታ የጦር መሳሪያዎች የተገኙ ሲሆን፣ ከእስር ቤቱን ለማምለጥና መሳሪያን ለማስገባት የሚያግዙ የምድር ውስጥ መተላለፊያ መንገዶችም ሊገኙ መቻላቸውን የእስር ቤቶቹ ሃላፊዎች ገልጸዋል።

ብራዚል ከአለማችን ሃገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን እስረኛ በመያዝ በአራተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ ወደ 600 ሺ የሚጠጉ እስረኞቹ በተለያዩ እስር ቤቶች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በእስር ቤቶች በሚፈጸሙ የእስር በርስ ግጭቶችን ወደ 500 የሚጠጉ እስረኞች በየአመቱ እንደሚሞቱና በቡድን የሚደረጉ ሁከቶች ለሃገሪቱ መንግስት ፈታኝ መሆኑን የእስር ቤት ሃላፊዎች ይገልጻሉ።