ኢሳት (ታህሳስ 25 ፥ 2009)
በባህርዳር ከተማ ነዋሪ የሆነ እስማዔል አህመድ የተባለ ኢትዮጵያዊ በወታደራዊ ዕዝ ወይም ኮማንድ ፖስቱ አባላት በመኖሪያ ቤቱ ደጃፍ ተገደለ። ከአራት ህጻናት ልጆቹና ከባለቤቱ ነጥለው ከመኖሪያ ቤቱ ካወጡት በኋላ ደጃፍ ላይ ገድለውት መሄዳቸውን የአካባቢው ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
መታወቂያ አሳይተው በመግባት ግድያውን የፈጸሙት የኮማንድ ፖስቱ አባላት፣ በቁጥር አራት መሆናቸውም ተመልክቷል። ኢስማዔል አህመት የተባለውና ነዋሪነቱ በባህርዳር ከተማ ነዋሪ የሆነው የ38 አመት ጎልማሳ በኮማንድ ፖስቱ ታጣቂዎች የተገደለው ሰኞ ምሽት ሶስት ሰዓት ላይ መሆኑም ተመልክቷል።
ታጣቂዎቹ የ38 አመቱን ነጋዴና የልጆች አባት መኖሪያ ቤቱ ገብተው ለምን እንደገደሉ የተገለጸ ነገር የለም። ግድያውን ፈጽመው ተመልሰው መሄዳቸውም ታውቋል።
መታወቂያ አሳይተው በመግባት እስማዔል አህመድን ህጻናቱ ልጆቹ ፊት በካቴና ካሰሩ በኋላ ይዘውት የወጡት የኮማንድ ፖስቱ አባላት በደጃፉ ላይ ገድለውት ሄደዋል።
የአባቱን የዘይት ፋብሪካ የሚቆጣጠረው ኢስማዔል አህመድ በኮማንድ ፖስቱ ለምን ዕርምጃ እንደተወሰደበት የታወቀ ነገር የለም። ኮማንድ በመኖሪያ ቤት ገብቶ ግድያ እንዲፈጸም ስልጣን እንደተሰጠው ታውቋል።
የአራት ህጻናት ልጆች አባት የሆነው የኢስማዔል አህመድ የቀብር ስነ-ስርዓት ማክሰኞ ታህሳስ 25 ቀን 2009 አም ድባንቄ በሚገኘው የሙስሊሞች መካነ-መቃብር ተፈጽሟል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) ለትግራይ ተወላጆች ያዘጋጀው ስብሰባ በባህርዳር ተካሄዷል።
በሳምንቱ መጨረሻ ቅዳሜና ዕሁድ በባህርዳር ኢትዮስታር ሆቴል በተካሄደውና ለትግራይ ተወላጆች በተዘጋጀው ስብሰባ በከተማዋ ሲኖሩ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። በተለይም የፊታችን ጥር 11 ፥ 2009 ከሚካሄደው የጥምቀት በዓል ጋር በተያያዘ የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወስዱ ማሳሰቢያ መሰጠቱና በወቅቱ ጉዳይም ውይይት መካሄዱ ታውቋል።