ታኅሣሥ ፳፬ (ሃያ አራት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰሞኑን በባህርዳር ከተማ በተካሄደው የብአዴን/ኢህአዲግ አባላት ስብሰባ ፣ ፓርቲው በ”ጥልቅ ታድሻለሁ!” ካለ በኋላም እየሰራ ባላቸው ስራዎች ህዝብን ከማማከር ይልቅ በራሱ ወስኖ መፈጸሙን እንዲያቆም በአባላቱ ተጠይቋል።
በአብዮታዊና ልማታዊ መስመር እራመዳለሁ የሚል መንግስት ከህዝብ ጋር የሚሰራውን ስራ ህዝብን በማማከር ማከናወን እንደሚገባው የገለጹት አባላት፤ብአዴን/ኢህአዴግ ለረዥም ጊዜ ከህዝብ ጋር ሲያጋጨው የኖረውን “እኔ አውቅልሃለሁ!” አሰራር አሁንም ደጋግሞ በመስራት ስህተቶችን እየፈጸመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አምባገነን መንግስታት ለህዝባቸው ክብር በመስጠት የብዙሃኑን ሃሳብ ከማዳመጥ ይልቅ በራስ ወስኖ ማከናወኑን መቀጠላቸው የተለመደ ክስተት መሆኑን የተናገሩት የብአዴን ፓርቲ አባላት፣ ፓርቲያቸው ህዝባዊነትን የተላበሰ መንግስት አለመሆኑን የሚያሳይ ምልክት በስራው እያሳየ ነው ይላሉ።
ብአዴን/ኢህአዴግ ለህዝብ እሰራለሁ የሚለውን ክንውን ለሚመለከታቸው የህብረተሰቡ አካላት እንኳን በአግባቡ የማያስተዋውቅበት ሁኔታ በተደጋጋሚ እየታየ መሆኑን አባላቱ ገልጸዋል፡፡ የፓርቲውን አባላት ቅሬታ ያቀረቡት የድርጅቱ አባል፣ ኢህአዴግ ውሳኔ ከወሰነ በሁዋላ፣ ለውይይት በሚል ስብሰባ የሚጠራን አባወራ ይመስላል ሲሉ የድርጅታቸውን የዲሞክራሲ ማእከላዊነት አሰራር ነቅፈዋል
በተያያዘ ዜና በብአዴን አባላት የተለያዩ ትችቶችን ሲያስተናግዱ የነበሩት የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች “አብዮታዊነት” የሚጠይቀውን ትልቅ ግብ እንዳላሳኩ በመድረኩ ተሳታፊዎች ተነግሯቸዋል፡፡ በትጥቅ ትግል ያስወገዱት የደርግ መንግስት “ለህዝቡ አልሰጠም!” ያሉትን የዲሞክራሲ ረሃብ ለማምጣት የተደቀነባቸውን ፈተና ማለፍ እንዳልቻሉ አባላቱ ለአመራሮች ተናግረዋል።
የኢህአዴግ መንግስት በደርግ መንግስት አልተተገበረም ብሎ መሳሪያ ያነሳበትን የዲሞክራሲ፣እኩልነትና የልማት ጥማት ጥያቄ ሊያሳካ አለመቻሉን በድፍረት የተናገሩት አባል፤ፓርቲው በሰራቸው ጥቂት ስራዎች በመኩራራት ከህዝቡ ጋር ያለውን ግንኙነት ከማጥበብ ይልቅ እያሰፋው መምጣቱን ተናግረዋል፡፡