ታኅሣሥ ፳፬ (ሃያ አራት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ በርካታ የነዳጅ ማደያዎች የቤንዚንና ናፍጣ እጥረት መታየቱን ወኪላችን ዘግቧል፡፡
ወጣ ገባ በሚል ሁኔታ ሲከሰት የቆየው የነዳጅ አቅርቦት ከያዝነው ወር መጀመሪያ አንስቶ ከዕለት ወደ ዕለት እጥረቱ እየተባባሰ መሄዱን አሽከርካሪዎች ለዘጋቢያችን ተናግረዋል፡፡ ከአሁን በፊት የነዳጅ እጥረት የሚከሰተው በወሩ መጨረሻ ከታሪፍ ጋር በተያያዘ መልኩ የገቢዎች ሰራተኞች ከማደያ ባለንብረቶች ጋር በሚያደርጉት ያልተገባ የጥቅም ትስስር ብቻ እንደነበር የሚገልጹት አሽከርካሪዎች፤ ከዚህ ወር መጀመሪያ አንስቶ በአንዳንድ ማደያዎች የታየው የነዳጅ እጥረት ባልተለመደ መልኩ ቀስ በቀስ እየሰፋ መሄዱ ስጋት እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል፡፡
በባህርዳር እና አካባቢ ከተሞች አንዳንድ ማደያዎች አገልግሎት መስጠት ካቆሙ ሳምንታት አስቆጥረዋል፡፡በተለይ የባህርዳር ከተማ አንጋፋ ማደያ የሆኑት የፓፒረስ እና ኖክ ማደያዎች ከሁለት ሳምንት በፊት ስራ አቁመዋል፡፡ የነዳጅ እጥረቱ በሃገሪቱ እየታየ ካለው የዶላር እጥረት ጋር ሊያያዝ ይችላል በማለት ሼፌሮች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።