በቻይና አለም አቀፍ የማራቶች ውድድር በሁለቱም ጾታዎች ኢትዮጵያውያን ድል ተቀዳጁ

ኢሳት (ታህሳስ 24 ፥ 2009)

ዕሁድ በቻይና በተካሄደ አለም አቀፍ የማራቶች ውድድር ኢትዮጵያውያን በሁለቱም ጾታዎች ተከታትለው በመግባት ድል ተቀዳጁ።

ከ30 ሺ በላይ ሰዎችና የተለያዩ ሃገራት አትሌቶች በተሳተፉበት በዚሁ የቤጂንግ የማራቶን ውድድር አትሌት ለሚ ብርሃኑ እና መሰረት መንግስቱ በአንደኝነት ማጠናቀቃቸውን የቻይና መገናኛ ብዙሃን ሰኞ ዘግበዋል።

ባለፈው አመት በዚሁ በአሜሪካ ቦስተን ከተማ ተካሄዶ በነበረው የማራቶን ውድድር አሸናፊ የነበረው አትሌት ለሚ፣ በ 2 ሰዓት 8 ደቂቃ በመግባት በመግባት የወርቅ ሜዳሊያን ያገኘ ሲሆን፣ አትሌት መሰረት መንግስቱ ደግሞ በሴቶች በሁለት ሰዓት ከ25 ደቂቃ በመግባት የወርቅ ተሸላሚ ለመሆን ችላለች።

ኢትዮጵያዊው አትሌት ለሚ ብርሃኑ በቦታው በኬንያ አትሌት ተይዞ የቆየውን የ2 ሰዓት ከስድስት ደቂቃ ሰዓት ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረትን ቢያደርግም ሳይሳካለት መቅረቱን ሲንሀአ በዘገባው አስነብቧል።