ኢሳት (ታህሳስ 24 ፥ 2009)
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሱዳን በምትዋሰንበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሸርቆሌ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በቤኒሻንጉል ነጻነት ንቅናቄና በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት ከ20 በላይ የጸጥታ አባላት መገደላቸውን የንቅናቄው አመራሮች ለኢሳት ገለጹ።
ከቀናት በፊት በተካሄደው በዚሁ ግጭት የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት የአጸፋ ዕርምጃ በትንሹ ስድስት ነዋሪዎች መገደላቸውንና ቁጥራቸው በአግባቡ የማይታወቅ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውንም የንቅናቄው አመራሮች አስረድተዋል።
የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው የደፈጣ ውጊያን ፈጽመዋል የተባሉት የንቅናቄው ታጣቂዎች ከሶስት ቀን በፊት በሁለት ተከታታይ ቀናት ባካሄዱት ጥቃት በመንግስት ሃይሎች ላይ ጉዳት መድረሱን የንቅናቄው ሃላፊ አቶ አብዱላ አላዲህ ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።
ከባለፈው ሃሙስ ጀምሮ በአካባቢው በተካሄደው በዚሁ ግጭት በመጀመሪያው ዙር 13 የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መሞታቸውንና ስድስቱ ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው ሃላፊው ገልጸዋል።
ለሁለተኛ ቀን በሸርቆሌ አጎራባች ስፍራዎች ሲካሄድ በነበረው ጥቃትም በትንሹ ስምንት የፌዴራልና ልዩ ሃይል አባላት ሊሞቱ መቻላቸውን የንቅናቄው አመራር የሆኑት አቶ አብዱላ አክለው አስታውቀዋል።
በዚሁ አካባቢ ከወራት በፊት መንግስት የሽብር ድርጊትን ሊፈጽሙ ሲሉ የነበሩት የንቅናቄው አባላት በቁጥጥር ስር ውለዋል ሲል መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ የንቅናቄው አባላት በፍርድ ሂደት ላይ እንደሚገኙም ለመረዳት ተችሏል።
በመንግስትና በንቅናቄው ታጣቂዎች መካከል ለተከታታይ ሲካሄድ የቆየውን ይህንኑ ግጭት ተከትሎ የፌዴራል አባላት በሁለት መንደሮች ላይ በወሰዱት የአፈና ዕርምጃ በትንሹ ስድስት ነዋሪዎች መገደላቸውን የንቅናቄው አመራር ገልጸዋል።
ለታጣቂ አባላቱ ድጋፍ ታደርጋላችሁ የተባሉት ቁጥራቸው ያልታወቀ የአካባቢው ነዋሪዎችም ለእስር መዳረጋቸውንና ድርጊቱ ውጥረት አንግሶ እንደሚገኝ ታውቋል።
በሳምንቱ መገባደጃ ቅዳሜ ድረስ ዘልቋል በተባለው በዚሁ ግጭት የተለያዩ መሳሪያዎችን ሊማረኩ መቻላቸውን የንቅናቄው አመራር የመሳሪያዎቹን አይነት በስም በመዘርዘር በቃለ-ምልልሳቸው ተናግረዋል።
መንጊ ተብሎ በሚጠራ ወረዳ አካባቢ ግጭቱ መቀጠሉን ያስታወቁት የንቅናቄው አመራር አቶ አብዱላ ድርጊቱ ተመሳሳይ ጥቃቶችን ሲፈጽም መቆየቱንም አከለው ገልጸዋል።