ኢሳት (ታህሳስ 20 ፥ 2009)
የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት በዶ/ር መረራ ጉዲና ላይ ለሁለተኛ ጊዜ በፖሊስ የተጠየቀን የተጨማሪ የ28 ቀን የምርመራ ጊዜ ሃሙስ ፈቀደ።
ምርመራውን እያካሄደ የሚገኘው ፖሊስ ዶ/ር መረራ በሽብር ወንጀል ድርጊት ስለመሳታፋቸው የተለያዩ ምርመራዎችን እያካሄደ መሆኑን ለችሎቱ ማስረዳቱን አዲስ ስታንዳርድ መጽሄት ዘግቧል። ቀደም ሲል ፖሊስ ዶር መረራን ያሰራቸው አስቸኳይ አዋጁን ተላልፈዋል በሚል የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ምርመራው የሽብር ወንጀል ሆኗል።
ይሁንና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ፖሊስ በሽብር ወንጀል እያካሄድኩባቸው ነው ያለውን ምርመራ በማስተባበል በተሰማሩበት የመምህርነት ሙያ ጸረ-ሁከትንና ጸረ-ሽብርተኝነትን ሲያስተምሩ መቆየታቸውን ለችሎቱ አስረድተዋል።
ሃሙስ ከሰዓት በአራዳ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተካሄደውን ችሎት ለመከታተል መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ ዲፕሎማቶችና የቤተሰብ አባላት እንዲሁም ደጋፊዎች ቢሰባሰቡም፣ የጸጥታ ሃይሎች ወደ ችሎቱ እንዳይገቡ ማድረጋቸው ታውቋል።
ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመከታተል ላይ የሚገኘው ወታደራዊ እዝ ዶ/ር መረራ ጉዲና በአውሮፓ በነበራቸው ጉብኝት ከአርበኞች ግንቦት ሰባት መሪ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ጋር ተገናኝተዋል በሚል ለእስር ሊዳረጉ መቻላቸውን መግለጹ ይታወሳል።
የዶክተር መራራ ጉዲናን ለእስር መዳረግ ተከትሎ የአውሮፓ ህብረት እንዲሁም የአሜሪካ መንግስት ድርጊቱ እንዳሳሰባቸው በመጥቀስ የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን ግልፅ እንዲያደርግ ሲያሳስቡ ቆይተዋል።
ሃሙስ ለሁለተኛ ጊዜ በተሰየመው ችሎት ላይ የተገኙት የዶ/ር መረራ ጉዲና ጠበቃዎች ደንበኛቸው በፖሊስ የቀረበን የሽብረተኛ ወንጀል ምርመራ አጥብቀው አስተባብለዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ከቀናት በፊት ለባንኮች ባስተላለፈው ትዛዝ ባንኮቹ ዶር መረራ ባለፈው አንድ አመት የነበራቸውን የገንዘብ ዝውውር ሪፖርት እንዲያቀርቡለት መጠየቁንም ለመረዳት ተችሏል።