ታኅሣሥ ፳ (ሃያ)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት የትውልድ ቦታ በሆነው በዳውንት ወረዳ ኩርባ ከተማ በሚገኙ 17 ቀበሌዎች የሚገኙ ወጣቶች፣ በጎንደር በኩል ወራሪ ጠላት መጥቷል በሚል እየተያዙ በግዳጅ ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑን የአይን እማኞች ገልጸዋል።
ወጣቶቹ ከሌሊቱ 8 እና 9 ሰአት ላይ እየታፈሱ በግዳጅ ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስዱ የሚደረግ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ በተደረገው 5 ዙር ስልጠና ከ300 በላይ ወጣቶች ሰልጥነዋል። ስልጠናውን የማይወስዱ በእድሜ የገፉ አርሶአደሮች የራሳቸውን አዝመራ ትተው ስልጠናውን የሚወስዱትን ወጣቶች አዝመራ እንዲሰበስቡ እየተገደዱ መሆኑን የአይን ምስክሮች ገልጸዋል ። ስልጠናውን የሚሰጡት በ1993 ዓም የተመለሱ ወታደሮች ናቸው ። የአካባቢ ሚሊሺያ ታጣቂዎችም በስልጠናው እንዲካተቱ ተደርጓል።
ወጣቶቹ ከስልጠና በሁዋላ ወደ ጎንደር እና ሌሎች ህዝባዊ አመጾች አሉባቸው በሚባሉ ቦታዎች ይሰማራሉ። በቅርቡ የተመረቁት አዳዲስ ሚሊሺዎች በሰሜን ጎንደር ከሚንቀሳቀሱ የነጻነት ሃይሎች ጋር ተዋግተው ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ታዋቂው የነጻነት አርበኛ ጎቤ መልኬን ጨምሮ ሌሎች የነጻነት ሃይሎች፣ ህወሃት የአንድ አካባቢው ሰዎችን እርስ በርስ ለማጋጨት የሚያደርገውን ሙከራ ህዝቡ እንዲያከሽፈው ጠይቀው ነበር።
ከዚሁ ከሰሜን ወሎ ዜና ሳንወጣ ከብሄር ብሄረሰቦች በአል ጋር በተያያዘ ከሳምንታት በፊት የታሰሩት የወልድያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እስካሁን አለመፈታታቸው ታውቋል፡፡ ያለምንም ጥያቄ እና ክስ እስር ቤት የሚገኙት ተማሪዎች እንዲፈቱ ወላጆቻቸው ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም መልስ የሚሰጣቸው አካል አላገኙም ፡፡