በአዲስ አበባ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ሊፈርሱ ነው

ታኅሣሥ ፳ (ሃያ)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- አዲስ በሚከለሰው ማስተር ፕላን ስም በአዲስ አበባ ከተማ እና በዙሪያዋ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የመኖሪያ ቤቶችን ለማፍረስ አዲስ ዘመቻ ሊጀመር መሆኑን መስተዳድሩ አስታውቋል።በዚህ ዘመቻ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ያለምንም ተተኪ ቤቶች ይፈናቀላሉ።

እንዲፈርሱ ትእዛዝ የተላለፈባቸው አካባቢዎች ፈረንሳይ፣ ካራ፣ የካ፣ አባዶ፣ ወሰን፣ ምኒሊክ፣ ኮተቤ፣ ሲኤምሲ፣ ቦሌ እና የካን የሚያዋስነው መስመር፣ መገናኛ፣ አዲስ አበባን ከኦሮሚያ ክልል የሚያዋስኑት አካባቢዎች የሚገኙ የጨረቃ ቤቶች በሙሉ እንዲፈርሱ መመሪያ ወጥቷል። በየካ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኙ ወረዳ 9፣ ወረዳ 10፣ ወረዳ 11 እና ወረዳ 13 ቤቶች እንዲፈርሱ ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማስታወቂያ ካወጣባቸው ከፈራሽ ወረዳዎች ዝርዝር ውስጥ ይገኙበታል።ለዘመናት ጎጆ ቀልሰው ሲኖሩ የነበሩ ዜጎች ለሚፈርስባቸው መኖሪያ ቤት እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ተለዋጭ ቦታ፣ የማረፊያ መጠለያ  እና ለንብረታቸው ካሳ አልተዘጋጀላቸውም።

ነዋሪዎች ሕጋዊ ሰነድ አስገቡ ተብለው በከተማዋ መስተዳድር ጥያቄ ቀርቦላቸው ህጋዊ ሰነዶችን ያስገቡ ቢሆንም፣መስተዳድሩ ግን ቤቶቹን ለማፍረስ ወስኖ የሚፈርሱ ቤቶችን ዝርዝር አውጥቷል።  በመስተዳድሩና በህዝብ መካከል ምንም አይነት አይነት ውይይት አልተደረገም።

በነፋስ ስልክ አካባቢ ካለምንም ካሳ ከ3 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን በማፈናቀል ቦታው ለቻይና ባለሃብቶች ተሽጧል።