ግብፅ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሃይሎች ስለመደገፏ የቀረበባትን  ቅሬታ በተመለከተ ይፋዊ ምላሽ ልትሰጥ ነው

ኢሳት (ታህሳስ 17 ፥ 2009)

የግብፅ መንግስት ኢትዮጵያ ላቀረበችው የተቃዋሚ ሃይሎችን ትደግፋላችሁ ቅሬታ ይፋዊ ምላሽ ለመስጠት በመዘጋጀት ላይ መሆኑ ሰኞ አስታወቀ።

ለአንድ አመት ያህል በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ የቆየውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ግብፅ ከዚሁ አመጽ ጋር ግንኙነት አላት ሲሉ ተቃውሞን ማቅረባቸው ይታወሳል።

ይህንና የግብፅ ባለስልጣናት ከኢትዮጵያ እኩል የቀረበውን ቅሬታ በማስተባበል ሃገሪቱ በሌላ ሃገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደማትገባ ምላሽ መስጠታቸውን ዴይሊ ኒውስ ኢጂፕት በዘገባው አውስቷል።

በሱዳን የመጀመሪያ ውጭ ጉብኝታቸውን ዕሁድ ያካሄዱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ሃገራቸው ከግብፅ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማስቀጠል መልካም ትብብር እያደረገች መሆኗን ለሳውዲ አረቢያው ሚድል ኢስት የዜና አውታር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ግብፅ በተለያዩ የሃገሪቱ ተቋማት በኩል በተለይ ለኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ድጋፍ ታደርጋለች ሲሉ በተደጋጋሚ ቅሬታን ማቅረባቸው ይታወሳል።

የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ለዚሁ ቅሬታ ይፋዊ ነው ያለውን ምላሽ በቅርቡ ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል።

ሁለቱ ሃገራት በአባይ ግድብ ግንባታ ምክንያት አለመግባባት ውስጥ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ እንዲያጤኑ የተመረጡ ሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎችም በዚሁ አለመግባባት ስራቸውን ሳይጀምሩ መቅረታቸው ተመልክቷል።

ኢትዮጵያ በግብፅ ላይ ያቀረበችውን ይህንኑ ቅሬታ ተከትሎ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ ሁለት ግብጻውያን ለእስር መዳረጋቸውን በሃገር ውስጥ ያሉ መገኛኛ ብዙሃን መዘገባቸው ይታወሳል። ይሁንና ኢትዮጵያም ሆነች ግብፅ በጉዳዩ ዙሪያ የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።