ታኅሣሥ ፲፯ (አሥራ ሠባት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከደርባን በ76 ኪ/ሜትር ላይ በምትገኘዋ ስኮት በርግ ከተማ በምትገኝ መንደር ውስጥ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 4 ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል፣ 8ቱ ደግሞ ቆስለዋል። 11 ሱቆቻቸውም ተዘርፈውባቸዋል። 1 የደቡብ አፍሪካ ፖሊስም ተገድሏል። አምስት ዘራፊዎችና ነፍሰ ገዳዮች በቁጥጥር ስር ከዋሉ በሁዋላ ፣ የዋስ መብታቸውን ለማስጠበቅ ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር። ኢትዮጵያውያኑ ድርጊቱን ለማውገዝና ፍትህ እንዲሰጣቸው ለመጠየቅ፣ ከአገሪቱ ዜጎች ጋር በጋራ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።
ኢትዮጵያውያኑ የንግድ ድርጅቶቻቸውን ዘግተው ተቃውሞአቸውን ያሰሙ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት ለጃንዋሪ 11፣ 2017 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ኢትዮጵያውያኑ ቀጠሮ መሰጠቱን ከሰሙ በሁዋላ ራሳቸውን እንዴት በጋር መከላከል እንደሚችሉ ውይይት አድርገዋል። በእለቱም ሁሉም ኢትዮጵያውያን በፍርድ ቤቱ ተገኝተው ተቃውሞአቸውን እንዲገልጹ ውሳኔ ላይ ደርሰዋል።
በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን ተደጋጋሚ ጥቃት በተመለከተ የአገሪቱ መንግስትም ሆነ አፍሪካ ህብረት ትኩረት ሰጥቶ ሲከታተለው አይታይም።