የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ለ12 አመቱ ታዳጊ ኢትዮጵያዊ አውስትራሊያዊ ደብዳቤ መልስ ሰጠ።

ታኅሣሥ ፲፯ (አሥራ ሠባት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የ12 አመቱ ታዳጊ ኢዮስያስ መላኩ በኢትዮጵያ ውስጥ እየደረሰ ያለውን ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰትና ግድያ፣ አፈናና እስራት የአውስትራሊያ መንግስት እንዲያወግዝ እንዲሁም በአገዛዙ ላይ እርምጃ እንዲወስድ የሚጠይቅ በድምጽ የተቀረጸ መልእክት ለአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ማልኮም ተርንበል ካስተላለፈ በሁዋላ፣ የጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ደብዳቤውን ለአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጁሊየ ቢሾፕ ማስተላለፉን የሚመለከት ምላሽ ተልኮለታል።

የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ በሰጠው ምላሽ ፣ በአዲስ አበባ ያለው የአውስትራሊያ ኢምባሲ በኢትዮጵያ ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ተቃውሞና አለመረጋጋት በትኩረት እየተከታተለው መሆኑን ጠቅሷል። በአገሪቱ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም እንዳሳሰበው ገልጿል።

የአውስትራሊያ መንግስት የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ስለሚፈጽሙት ግድያ፣ እስርና ማንገላታት በደንብ እንደሚያውቅ በደብዳቤው ጠቅሶ፣ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን  በማንሳት በቀጥታ ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር በየጊዜው እንደሚነጋገርበት አክሏል።

አውስትራሊያ የኢትዮጵያ መንግስት ለህግ የበላይነት እንዲገዛ እንዲሁም ማንኛውንም ሰብአዊ መብቶች እንዲያከብር፣ ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻ እንዲገልጹና በነጻነት እንዲሰበሰቡ መወትወቱን እንደሚቀጥል የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ በደብዳቤው ገልጿል።

የታዋቂዋ የሰብአዊ መብት ተሟጋች የወ/ሮ ሃና ለገሰ ልጅ የሆነው እዮስያስ የ6ኛ ክፍል ተማሪ ነው። እዮስያስ በደብዳቤው፣ እናቱና እሱ በኢትዮጵያ የሚደርሰው የጅምላ ፍጅት እንዲቆም በየእለቱ እንደሚጸልዩ ገልጿል። የአንድ አገር መሪ የሚንከባከብ፣ የተማረ ፣ ሰዎችን የሚያከብር እና ጎበዝ መሆን ቢኖርበትም በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው የሚለው ኢዮስያስ፣ የአውስትራሊያ መንግስት እና ጠ/ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያውያን ጎን በመቆም በአገሪቱ የሚደርሰውን ፍጅት እንዲያስቆሙ ጠይቆ ነበር።