በደቡብ ኦሞ ውጥረቱ እንዳለ መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ

ታኅሣሥ ፲፬ (አሥራ አራት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ከጥር ወር 2007 ዓ.ም ጀምሮ የሃመር ወጣቶች ‹‹ከዱር አራዊት በታች መታየት የለብንም›› በማለት የጀመሩት የተቃውሞ እንቅስቃሴ አሁንም መፍትሄ ባለማግኘቱ ውጥረቱ እንዳለ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ። የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት በአስቸኳይ አዋጅ ስም ጥያቄውን ለማፈን የሚያደርገው እንቅስቃሴ ህዝቡን ለበለጠ አለመረጋጋት መዳረጉን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

“ተቃውሞው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ሰራተኞች ፣ የመከላከያና ፌደራል ፖሊስ አባላት ተገድለዋል። የቀድሞው የዞኑ ም/ል አስተዳዳሪ አቶ አወቀ አይኬ  መኪና በጥይት ተመቷል፡፡ ዞኑን ከወረዳዎች የሚያገናኙ መንገዶች ተዘግተዋል፣ በሃመርና አርቦሬ ብሄረሰቦች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ተደርጎ  ከሁለቱም ወገን ዜጎች አልቀዋል” በማለት የሚያስታውሱት ነዋሪዎች፣ ባለፉት 3 ወራት ብቻ 3 ፖሊሶች ተገድለዋል፣  የፖሊስ ጣቢያ ተደምስሷል፣ የቱሪስት መኪና በጥይት ተመቷል፡፡ዞኑን ከስኳር ፐሮጄክቶች የሚገናኘው መንገድም ተዘግቷል። በአካባቢው የሰፈረው ሰራዊት አሁንም ችግሩን ከማባባስ ውጭ መፍትሄ ሊያመጣ አልቻለም።

በዞኑ ዋና ከተማ ጅንካ ደግሞ በከተማው ከሰፈረው ሰራዊት  የከዱ 3 የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወዳልታወቀ ቦታ ሸኝታችኋል በሚል ሦስት ወጣቶች ታስረው ተለቀዋል። ይህንኑ ተከትሎ  የግል መጠቀሚያ የሆኑትን ሞተር ብስክሌቶች ጨምሮ ባጃጅ መኪኖች ከምሽቱ 3፡00 በኋላ እንዳይንቀሳቀስ በመደረጉ በባጃጅ ሥራ ቤተሰብ በሚያስተዳድሩ ወጣቶችና በታጣቂዎች መካከል አለመግባባቱ ጨምሯል። በርካታ ወጣቶችም በየጊዜው እየተያዙ ይታሰራሉ።

ሰሞኑን በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶችን ለመጠየቅ ወደ እስር ቤት ያመሩ ከ30 ያላነሱ መምህራን እስረኞችን “ መጠየቅ አትችሉም” በመባላቸው ከፖሊሶች ጋር ተጋጭተው የነበረ ሲሆን፣ በመጨረሻ በአቋማቸው ጸንተው እንዲጠይቁ ተፈቅዶላቸዋል።