ኢሳት (ታህሳስ 14 ፥ 2009)
ኢትዮጵያዊው የኦሎምፒክ ጀግና ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ከዚህ አለም በሞት ተለየ።
አትሌት ምሩጽ ይፍጠር በ72 አመት ዕድሜው ከዚህ አለም በሞት የተለየው በስደት በሚኖርበት ካናዳ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ነው።
የኦሎምፒክ ጀግና ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር በ1972 በሞስኮ በተደረገው ውድድር በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትሮች ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ለኢትዮጵያ ያስገኘ ድንቅ አትሌት ነበር።
ማርሽ ቀያሪው በሚል የሚታወቀው ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር በ1964 ዓም በሙኒክ ኦሎምፒክ በ10 ሺ ሜትር ለሃገሩ የነሃስ ሜዳሊያ አስገኝቷል።
ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር በሞስኮ በ5ሺ እና 10 ሺ ሜትሮች የወርቅ ሜዳሊያ ለሃገሩ በማስመዝገቡ እና ላስገኘው ድርብ ድል በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ መንግስት የልዩ ሜዳሊያ ተሸላሚ አድጎታል።
ጀግናው አትሌት ምሩፅ ይፍጠር በ1990 ዓም ሃገሪቱ በመልቀቅ ወደካናዳ የተሰደደው በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ በዘረኝነት ምክንያት ሰዎች ከስራ ሲያፈናቅልና ቤተሰባቸው ሲቸገሩ በማየቱ መሆኑን ለኒውዮርክ ታይምስ በወቅቱ መግለጹ ይታወሳል።
ምሩጽ ይፍጠር የ3 ልጆች አባት የነበረ ሲሆን፣ የቀብር ስነስርዓቱ በኢትዮጵያ እንደሚፈጸም ከቤተሰቦቹ ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ (ኢሳት) በአትሌት ምሩፅ ይፍጠር ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን በመግለጽ ለመላው ህዝብና ቤተሰቡ መጽናትን ይመኛል።