ታኅሣሥ ፲፫ (አሥራ ሦስት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው እሁድ – ታህሳስ 9/2009 ዓ.ም አቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ከደቡብ ክልል ፕሬዝዳንትና ከደህዲን አመራር አባላት ጋር በደቡብ ኦሞ የሚገኙትን የኩራዝ አንድና ሁለት የስኳር ፕሮጀክትና የጂንካን ዓለምአቀፍ አይሮፕላን ማረፊያ መጎብኘታቸውንና በዚያው ቀን ተመልሰው አዲስ አበባ መሄዳቸውን የገለጹት ምንጮች፣ በዚህ ጉብኝታቸው የዞኑ ፖሊሶች እንዳይገኙ ተደርጓል።
የአቶ ሃይለማርያም ጉብኝት በከፍተኛ ሚስጢር ተይዞ እንደነበርና ከደህንነቶች በቀር ማንም የዞን ባለሥልጣናትም ሆኑ የዞኑ ነዋሪዎች ስለጉብኝቱ ያወቁትና የሰሙት ከሁለት ቀን በፊት ዓርብ ዕለት መሆኑን የሚገልጹት ምንጮች፣ ከጂንካ ከተማ ውጪ ያለው የአካባቢው ነዋሪዎች ስለጉብኝቱ ምንም መረጃ አልነበራቸውም።
ነዋሪዎች “ በጅንካ ከሚገኙ ባለሥልጣናት የተወሰኑት ተመርጠው፣ የዞኑና ከተማው ፖሊሶች እንዳይገኙ ተደርጎ ፣ ከከተማው ነዋሪ የዞኑን አስተዳዳሪና ደህንነቶች ጨምሮ ከከተማው ሠላሳ ሰዎችና የራሳችን ናቸው የሚሏቸው ጥቂት ነዋሪዎችና ‹የአገር ሽማግሌዎች › ብቻ በተገኙበት፣ግን ከከተማው ውጪ ያሉ ‹የእነርሱ ›የሆኑና በህዝብ ያልተወከሉና ህዝቡን የማይወክሉ ሰዎች በመሰብሰብ የከተማው ነዋሪ ከቤቱ እንዳይወጣ ተደርጎ ሳናያቸው መመለሳቸው ጉብኝቱን አስገራሚ ያደርገዋል፤” ብለዋል።
በተለይ የዞኑና የከተማው ፖሊሶች በቦታው እንዳይገኙ መደረጉና በፌደራል ፖሊስ ብቻ እንዲጠበቁ መደረጋቸው፣ በፖሊሶች ዘንድ ከፍተኛ ጥያቄና ቁጭት መፍጠሩን ፣ የፖሊስ አባላትም በጉዳዩ እርስ በርስ መነጋገር መጀመራቸውን፣ እንዲሁም በተፈጠረው ሁኔታ ማዘናቸውን ና አለመተማመኑ እየሰፋ መምጣቱን ፖሊሶች በግልጽ እየተናገሩ ነው።
ይህ የዞኑና የከተማው ፖሊሶች በኮማንድ ፖስት ከክልልና ፌደራል ከመጡት ታጣቂዎች ጋር ለመግባባት በ መቸገራቸውና እነርሱ እንዲወስዱ የሚፈልጉትን እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ ካለመሆናቸው ጋር ተያይዞ የተደረገ የማግለል ስራ ሊሆን እንደሚችል ምንጮች ይገልጻሉ። አቶ ሃይለማርያም የጎበኙዋቸው የስኳር ፕሮጀክቶች ከመጠናቀቂያ ጊዜያቸው በእጅጉ የዘገዩ ሲሆን፣ አቶ ሃይለማርያም ግን በሁለት ወራት ይጠናቀቃል ሲሉ ተናግረዋል።
ከህወሃት ጋር ቁርኝት እንዳለውና በኢትዮጵያ የሚገነቡ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን የሚወስደው ‹‹አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ›› በከተማው የሚገነባው አየር ማረፊያ ደረጃውን ያልጠበቀና የግንባታው ጊዜም የተጓተተ መሆኑን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
በጂንካ ከተማ ህዝባዊ ተቃውሞ ያስነሳሉ የተባሉ የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት ም/ል ሊቀመንበር መምህር አለማየሁን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ።