የአፋሯ አርቲስትና አክቲቪስት ማፋራ መሀመድ ላሌ ተፈታች

ታኅሣሥ ፲፫ (አሥራ  ሦስት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ከህዝባዊ አመጹ ጋር በተያያዘ ላለፉት ወራት  ታስራ የቆየችው የአፋሯ አርቲስትና አክቲቪስት ማፋራ መሀመድ ላሌ ከትናትን በስቲያ  ከእስር ተፈታች።

በአውሮፓ የአፋር ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ሰብሳቢ አቶ ገአስ አህመድ በተለይ ለኢሳት እንደገለጹት ከዱብቲ ከተማ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ተቃውሞ አስነስተሻል ተብላ ለወራት ለእስር የተዳረገችው አርቲስት ማፋራ  የተፈታችው በዋስ ነው።

ፍርድ ቤት በዋስ እንድትፈታ ሲወስን አርቲስት ማፋራ “ ምንም ዓይነት ወንጀል ስለልሠራሁ  ዋስ አልጠራም! በነጻ መፈታ አለብኝ” በማለት የተቃወመች ቢሆንም  ፍርድ ቤቱ በግዳጅ ዋስ መጥራት እንዳለባት ውሳኔውን በማጽናቱ በዋስ መለቀቋን አቶ ገአስ ገልጸዋል። በኦሮሚያና አማራ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞው ባየለበት ወቅት በአፋር ክልል የዱብቲ አስተዳደር ስብሰባ በመጥራት ተሰብሳቢዎቹ  በሁለቱ ክልሎች የተነሱትን አመጾች በመቃወም ሰልፍ እንዲያደርጉ ግፊት በሚያደርግበት ወቅት ነበር ከተሰብሳቢዎቹ አንዷ የሆነችው አርቲስና አክቲቪስት ማፋራ  ሀሳቡን በመቃወም ስብሰባውን ረግጣ የወጣችው።

ማፋራ በወቅቱ  ስብሰባው ላይ ባሰማችው ተቃውሞ  ወንድሞቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግድያና አፈና መቃወም ሲገባን ይባስ ብሎ  ህዝባዊ አመጹን ተቃውማችሁ ሰልፍ ውጡ መባሉ የአፋርን ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ለማጋጬት የተደረገ ሴራ በመሆኑ አልቀበለውም በማለት ነበር አቋሟን ገልጻ ከአዳራሹ የወጣችው። በዚህም የማፋራ ተቃውሞ ምክንያት የመስተዳድሩ እቅድ ሳይሳካ ስብሰባው ተበተነ።

በዚህ የተበሳጩት የአካባቢው ሹመኞችም  ሕዝብን ለአመጽ በማነሳሳት በማለት ነበር አርቲስትና አክቲቪስ ማፋራን ወዲያውኑ በደህንነቶች አሳፍነው ያስወሰዷት። የማፋራን መታሰር ተከትሎ የአፋር ሰብ አዊ መብቶች ጉባኤና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በተለይ በኢሳት በመቅረብ በተደጋጋሚ ድምጻቸውን ሲያሰሙ መቆየታቸው ይታወቃል። በመሆኑም ላለፉት ወራት ያለ ጠያቂ  በእስር ቤት ስትሰቃይ የቆየችው አርቲስት ማፋራ  በስተመጨረሻ በዋስትና ለመፈታት በቅታለች።

አርቲስትና አክቲቪስት ማፋራ ከልጅነቷ ጀምራ ለአፋር ሕዝብ መብት መከበር ያለመታከት ድምጿን በማሰማቷ በተለይ ባለፉት የኢህአዴግ አመታት በተደጋጋሚ ለእስርና ለእንግልት ስትዳረግ ቆይታለች። የተቃዋሚ ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እስከመሆን የደረሰችው አክቲቪስ ማፋራ ያሳለፈችው የትግል ታሪክ ትልቅ ጥራዝ ያለው መጽሐፍ የሚወጣው ቢሆንም  በህወኃት የሚዘወሩት የክልሉ ሚዲያዎች  ሆነ ብለው ሽፋን እንዳታገኝ አድርገዋት ቆይተዋል።