ታኅሣሥ ፲፫ (አሥራ ሦስት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከሕግ አግባብ ውጪ ከመኖሪያ ቤታቸው ከስራ ገበታቸው እንዲሁም ከመንገድ ላይ እየተያዙ ከአንድ ወር በላይ በእስር ሲንገላቱ ከነበሩት ጋዜጠኞች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት መካከል የተወሰኑት ተፈተዋል።
የዞን 9 አምደመረብ ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ፣ የበይነ መረብ አምደኛው ስዩም ተሾመ፣ ወጣት ብሌን መስፍን፣ ደራሲና ጋዜጠኛ ሰሎሞን ስዩም፣ መምህር አበበ አካሉ እና ወጣት እያስፔድ ተስፋዬ እና ሌሎችም የኅሊና እስረኞች ተለቀው ወደ መኖሪያ ቤታቸው መመለሳቸውን ዞን 9 በፌስ ቡክ ገፁ ዘግቦታል።
ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የመብት ጥሰት አስመልክቶ ለቪኦኤ አማርኛ ዜና አገልግሎት በሰጠው ቃለመጠይቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተችተሃል በሚል ከመኖሪያ ቤቱ አካባቢ በኮማንድ ፖስቱ ተይዞ ከአርባ ቀናት በላይ በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማእከል ውስጥ ቆይቷል። ወጣት ጋዜጠኞች ኤሊያስ ገብሩ፣ አናኒያ ሶሪ እና የቀድሞው አንድነት ፓርቲ አመራር የነበረው አቶ ዳንኤል ሺበሺ አሁንም ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሶስቱ የለውጥ አቀንቃኞች ከመንገድ ላይ ታፍሰው የታሰሩ ሲሆን ከቤተሰባቸውና ከጠበቃቸው ጋር እንዳይገናኙም ተደረገዋል።
ኮማንድ ፖስቱ ቁጥራቸው 10 ሽህ የሚሆኑ ወጣቶችን ለቅቂያለሁ ቢልም አሁንም አያሌ የለውጥ አቀንቃኝ ናቸው የተባሉ ወጣቶች በኮማንድ ፖስቱ ተይዘው በአዋሽ አርባ፣ በብርሸለቆ፣ አላጌ ግብርና ማሰልጠኛ ማእከል፣ ዝዋይ፣ በሸዋ ሮቢት በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያ እስር ቤቶች እና ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካንፖች ውስጥ ታስረው ወታደራዊ ቅጣቶች፣ ሰቆቃ ቶርቸር፣ አካላዊ ጥቃቶች ይፈጸምባቸዋል።
ኢሰብዓዊ የሆነውን ስቃይ እና ሰቆቃ መቋቋም ተስኗቸው ሕይወታቸው ያጡም አሉ።