በሽብርተኛ ወንጀል ክስ የሚመሰረትባቸው ጋዜጠኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑን ሲፒጄ አስታወቀ

ኢሳት (ታህሳስ 13 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ ለእስር የሚዳረጉና የሽብርተኛ ወንጀል ክስ የሚመሰረትባቸው ጋዜጠኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣት አሳሳቢ መሆኑን አንድ አለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት አስታወቀ።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትላንት ረቡዕ በሁለት ጋዜጠኞች ላይ በሽብርተኛ ወንጀል ክስ ያስተላለፈው የጥፋተኝነት ብይን በኢትዮጵያ ያለውን የጋዜጠኞች አፈና አመላካች እንደሆነ ኮሚቴ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስትስ (ሲፒጄ) ገልጿል።

በድርጅቱ ምክትል ሃላፊ ሮበርት ማሆኒ በጋዜጠኞች ካሊድ ሞሃመድና ዳርሴማ ሶሪ እንዲሁም በሌሎች ጋዜጠኞች ላይ እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ በአስቸኳይ እንዲቆም ሲሉ ለመንግስት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለቱ ጋዜጠኞችን ጨምሮ 20 ተከሳሾች በተመሰረተባቸው የሽብርተኛ ወንጀል ክስ ረቡዕ ጥፋተኛ ናቸው ሲል ብይን መስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል።

ከአንድ አመት በፊት ለእስር ተዳርገው የነበሩ ሁለቱ ጋዜጠኞች በራዲዮ ቢላል በአዘጋጅነት ሲሰሩ ነብር። ከሳሽ አቃቤ ህግ ጋዜጠኞቹ በሃገር ውስጥ ሲካሄድ የነበረውን የሙስሊሙ ማህበረሰብ በከለላነት በመጠቀም የጽንፈኛ አስተሳሰብን ሲያሰራጩ ነበር ሲል በክሱ አመልክቷል።

ከሌሎች 18 ተከሳሾች ጋር በጋራ ህገ-መንግስቱን በሃይል ለመገልበጥ ተንቀሳቅሰዋል የሚል ክስ ጭምር ተመስርቶባቸው የነበሩት ጋዜጠኛ ካሊድ ሞሃመድና ዳርሴማ ሶሪ ከ16 ጋዜጠኞች ጋር በኢትዮጵያ በእስር ላይ እንደሚገኙም ታውቋል።

የዘንድሮውን አመታዊ ሪፖርቱን በቅርቡ አውጥቶ የነበረው ሲፒጄ፣ ኢትዮጵያ በአለም የከፋ የጋዜጠኞች አሳሪ ተደርገው ከተፈረጁ አምስት ሃገራት መካከል አንዷ መሆኗን ይፋ አድርጓል።

በርካታ አለም አቀፍ የሰብዓዊ እና የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች ኢትዮጵያ ለመገናኛ ብዙሃን ምቹ ያልሆነች ሃገር እየሆነች መምጣቷን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።

በአሁኑ ወቅት ለእስር ተዳርገው ከሚገኙ 16 ጋዜጠኞች መካከል የረጅም ጊዜ የእስር ቅጣት የተላለፈባቸውና ያለምንም ክስ የሚገኙ እንዳሉም ተመልክቷል።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሁለቱ ጋዜጠኞችና በ18ቱ ሌሎች ተከሳሾች ላይ የፍርድ ውሳኔን ለመስጠት ለቀጣዩ ሳምንት ቀጠሮ መያዙም ታውቋል።