ከቱሪስት ዘርፍ የሚገኘው ገቢ መቀነስ እንዳሳሰበው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ

ኢሳት (ታህሳስ 13 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ ጉብኝት የሚያደርጉ የቱሪስቶች ቁጥር መቀነስና የሚገኘው ገቢ መሻሻል አለማሳየቱ ስጋት ማሳደሩን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሃገሪቱ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙ አለም አቀፍ ቱሪስቶች ቁጥር በከፍተኛ መጠን መቀነሱ በተደጋጋሚ መገለጹ ይታወሳል።

በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የሚኒስቴሩ ባለስልጣናት ባለፉት ሶስት ወራት የጎብኚዎች ቁጥር እየቀነሰ በመሄድ ላይ መሆኑን ለሃገር ውስጥ መገኛኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

ባለፈው አመት ከ900 ሺ በላይ ቱሪስቶች በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች ጉብኝት አድርገው እንደነበር ያወሳው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከዘርፉ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውቋል።

ይሁንና ከቱሪዝም የተገኘው የባለፈው አመት ገቢ በተያዘው በጀት አመት በከፍተኛ ሁኔታ ያሽቆለቁላል ተብሎ ተሰግቷል። ከ400 ሚሊዮን ዶላር የሚበልጥ ገቢ ሊቀንስ እንደሚችል ስጋት መኖሩን አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል።

ሃገሪቱ የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር መሻሻል ባለማሳየቱ ምክንያት በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽ/ቤቶች ቱሪስቶችን ለማሳመን የማግባባት ስራ እንደሚያከናውኑ መንግስት ትዕዛዝ መስጠቱም ታውቋል።

ከቱሪዝም እና ከውጭ ንግድ ገቢ እየተገኘ ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በከፍተኛ መጠን እየቀነሰ በመሆኑን በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን የአለም ባንክና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ይገልጻሉ።

የብሪታኒያና የአሜሪካ መንግስታት ዜጎቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ በተደጋጋሚ የጣሉት እገዳ በተለይ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ጉዳት ማድረሱ ተነግሯል።

የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዜጎቹ ያሰራጨውን የጉዞ ማሳሰቢያ ተከትሎ በርካታ የሃገሪቱ አስጎብኚ ተቋማት ለፈረንጆቹ አዲስ አመት የያዙትን እቅድ ሙሉ ለሙሉ መሰረዛቸው ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የብሪታኒያ መንግስት ዜጎቹ ወደ አማራ ክልል ሶስት ዞኖች እጅግ አስፈላጊ ካለሆነ በስተቀር እንዳይጓዙ ያሳሰበበት መግለጫ ሃሙስ ቀጣይ እንዲሆን ወስኗል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዜጎች ተመሳሳይ የጉዞ ማሳሰቢያን ተግባራዊ አድርጎ ይገኛል። ድርጊቱ ወደ ኢትዮጵያ በሚጓዙ ቱሪስቶች ላይ ስጋትን ማሰደሩን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።