በግል ባንኮች ያላቸውን የባለቤትነት ድርሻ ሸጠው እንዲወጡ የተገደዱ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከመሬት ጋር የተያያዘ መመሪያ እየተዘጋጀላቸው መሆኑ ተገለጸ

ኢሳት (ታህሳስ 13 ፥ 2009)

በቅርቡ በኢትዮጵያ የግል ባንኮች ያላቸውን የባለቤትነት ድርሻ ሸጠው እንዲወጡ የተገደዱት ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ከመሬት ጋር በተያያዘም ተጨማሪ መመሪያ እየተዘጋጀቸው መሆኑን ምንጮች ለኢሳት ገለጹ።

ለዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን በተሰጠ ልዩ መብት ቤት የሰሩ እንዳይሸጡ፣ ከእነርሱም የገዙ ስም እንዳያዛውሩ ዕገዳ መጣሉን መረዳት ተችሏል። ይህም ከቅርቡ መመሪያ ጋር የተያያዘ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

የውጭ ሃገር ዜግነት የያዙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተሰጣቸው ልዩ መብት የሰሩትን ቤት እንዳይሸጡ፣ ከእነርሱም ቤት የገዙ ስም እንዳያዛውሩ የተደረገበት ምክንያት አልተገለጸም። በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ፖሊሲ እንደሚወጣም እየተነገረ ይገኛል።

የተባለው ፖሊሲ እስኪወጣ ንብረት የመሸጥና የመለወጡ ሂደት ተጓቷል።  አስቀድመው ግዢ የፈጸሙና ስም ያላዛወሩትን በተመለከተ ሂደቱ በመጓተት ላይ እንደሆነም መረዳት ተችሏል።

ስልጣን ላይ ያለው መንግስት በባንክና ኢንሹራንስ ዘርፍ ኢንቨስት ያደረጉ ኢትዮጵያውያንን ከመስኩ ለማስወጣት የተደረሰበት ውሳኔና አሁንም በማይንቀሳቀስ ንብረቶች ላይ ተጨማሪ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን ከምን የተነሳ እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም።

በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አገኘዋለሁ ብሎ የጠበቀው የፖለቲካ ድጋፍና የውጭ ምንዛሪ ፍሰት አለመሳካቱ ለእርምጃዎቹ አስተዋጽዖ ሳያደርግ እንዳልቀረ ተመልክቷል።

በሌላም በኩል የግል ባንኮች ካፒታላቸውን ወደ ግማሽ ቢሊዮን እንዲያሳድግ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ በወራት ውስጥ የሚያበቃ በመሆኑ፣ የትውልደ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ በመገደብ፣ አንዳንድ ባንኮች ከመስኩ ለማስወጣት የታለመ ሊሆን እንደሚችልም ጥርጣሬ አለ።