ታኅሣሥ ፲፪ (አሥራ ሁለት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሰሜን ጎንደር የነጻነት ሃይሎች፣ አርሶአደሮችና የታጠቁ ሃይሎች በገዢው ፓርቲ ወታደሮች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት መጨመሩን ተከትሎ፣ አገዛዙ ሰራባ ላይ 46ኛ ክፍለ ጦር ለማቋቋምና ሰራባን የጦር መሳልጠኛ ለማድረግ ማሰቡንም ምንጮች ገልጸዋል።
ሰራባ የሚገነባው ክፍለጦር፣ አዘዞ ሎዛ ማሪያም ላይ ያለው 24ኛው ክፍለ ጦር ፈርሶ ይሁን ወይም ተጨማሪ አልታወቀም። በዞኑ ወታደራዊ ፍተሻው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ ፍተሻው በአዘዞ ፣ ሰራባ፣ ነጋዴ ባህርና ሸህዲ ላይ ይካሄዳል።
የአገዛዙ ወታደራዊ አዛዦች፣ በአሁኑ ሰአት ራሳቸውን የሰወሩትን የነጻነት ሃይሎች ያሉበትን ቦታ ለማወቅ በሽምግልና ስም እንቅስቃሴ ጀምረዋል። አዲሱ በሽምግልና ስም የሚካሄደው እንቅስቃሴ በአንድ በኩል ከተሳካ በሽምግልና ስም አግባብቶ በምህረት እጅ በማሰጠት ታጋዮችን ለመያዝ፣ ካልተሳካ ደግሞ ሽማግሌዎች የታጋዮቹ አመራሮች ያሉበትን ቦታ እንዲጠቁሙ ለማድረግ መሆኑን ምንጮች ይገልጻሉ።
በቅርቡ ተደርገው በነበሩት ተደጋጋሚ ውጊያዎች ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት፣ የጸረ ሽምቅ አዛዡን ጨምሮ በጦር ሜዳ የተሰለፉትን ተዋጊዎቹን ሳይቀር ይዞ እያሰረ ነው።