ታኅሣሥ ፲፪ (አሥራ ሁለት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከየመን በህገወጥ መንገድ ተይዘው ለህወሃት/ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ተላልፈው ከተሰጠቡት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከሰኔ 2፣ 2014 ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ትናንት ማክሰኞ በእንግሊዝ ፓርላማ ጉዳያቸው የመወያያ ርእስ ሆኖ የቀረበ ሲሆን፣ በስብሰባው ላይ የተሳተፉት የፓርላማ አባላት በሙሉ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ ላይ አስፈላጊውን ጫና ፈጥሮ አቶ አንዳርጋቸው የሚለቀቁበትን መንገድ እንዲፈልጉ ጠይቀዋል።
ከአንድ ሰአት በላይ በወሰደው በዚህ ክርክር አቶ አንዳርጋቸው በእስር ቤት ስለደረሰበት ጉዳት፣ ከቤተሰቦቹ ፣ ከህግ አማካሪዎችና በአጠቃላይ በህገ ወጥ መንገድ ተላልፎ ስለመሰጡ ሰፊ ገለጻ ተደርጓል። የፓርላማ አባላቱ በየተራ እየተነሱ የአቶ አንዳርጋቸውን ጉዳይ እያነሱ የተናገሩ ሲሆን፣ የአገራቸው መንግስት ማንኛውንም መንገድ ተጠቅሞ ችግሩ እልባት እንዲያገኝ አሳስበዋል።
ለጥያቄዎቹ መልስ የሰጡት የካቢኔ አባሉ ፣ የአቶ አንዳርጋቸውን ጉዳይ በቅርብ እየተከታተሉት መሆኑን ገልጸዋል። በቅርቡ የእንግሊዝ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ እንዲጎበኛቸው መደረጉንና እርሳቸውም በጥሩ መንፈስና ጥንካሬ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
አቶ አንዳርጋቸው እንዲፈቱ የእንግሊዝ መንግስት በቀጥታ የማይጠይቀው ውጤት ያመጣል የሚል እምነት ስለሌላቸው መሆኑን የገለጹት ባለስልጣኑ፣ ይሁን እንጅ ጥረታቸውን በውስጥ የዲፕሎማሲ መስመር እንደሚጥሉና በሚቀጥለው ወር መጨረሻ ወደ ኢትዮጵያ ሲያመሩ የአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው የሚወያዩበት እንደሚሆን ተናግረዋል።
የእንግሊዝ የፓርላማ አባላት በአቶ አንዳርጋቸውና በሌሎች አገራት እስር ቤቶች በሚገኙ የእንግሊዝ ዜግነት ባላቸው ታዋቂ ሰዎች ላይ በዚህ ደረጃ ሰፊ ሰአት ሰጥተው ሲወያዩ ይህ የመጀመሪያ ነው።