ታኅሣሥ ፲፪ (አሥራ ሁለት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- እንደ ተባባሩት መንግስታት ድርጅት የጥናት ሪፖርት መረጃ መሰረት በፈረንጆች አቆጣጠር በ2016፣ 107 ሽህ 532 አጠቃላይ ስደተኞች ወደ የመን የገቡ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ከተቀሰቀሰው ሕዝባዊ አመጽ በኋላ ወደ የመን የገቡ ኢትዮጵያዊን ስደተኞች ቁጥር 92 ሽህ 768 ወይም 83 በመቶ የሚሆነውን ይይዛል።
ካለፈው መስከረም ወር ወዲህ ብቻ ቁጥራቸው 3 ሽህ 109 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን መነሻቸውን ከየመን በማድረግ ወደ ጣሊያን ገብተዋል። ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅትየገቡት 2 ሽህ 634 እንደነበርም ድርጅቱ አስታውሶ፣ አብዛሃኞቹ ወደ አውሮፓ የሚገቡ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ኤርትራዊ በማለት ዜግነት ይቀይራሉ ብሏል። ከኢትዮጵያዊያን በመቀጠል 18 ሽህ 736 ሶማሊያዊያን ስደተኞች በተመሳሳይ በጅቡቲ ኦቦክ፣ በፑትላንድ ቦሳሶ በባህር አድርገው በሕገወጥ ደላሎች አማካኝነት የመን ይገባሉ። በተመሳሳይም ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በህገወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ ከሚገቡ ዜጎች ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚወስዱ ሲሆን በዓመት ውስጥ ከ10 ሽህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ደቡብ አፍሪካ ገብተው ጥገኝነት ይጠይቃሉ።
በቅርቡ በመላው ኢትዮጵያ ከተነሳው ተቃውሞ በኋላ የተሰደዱ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች 95-98% የሚሆነውን ቁጥር ይሸፍናሉ። ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በብዛት አገሪቱን መልቀቃቸው በአገርቱ ያለውን የጅምላ እስራት፣ ግድያ እና አፈና የሚያሳይ መሆኑም በጥናቱ ተመልክቷል። ስደተኞቹ ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው በረሃዎችን በእግር በመጓዝ ከየመን ወደ ሳኡዲ አረቢያ የሚያቀኑ ሲሆን ፣ በጉዞ ላይ እያሉ አብዛሃኞቹ የተለያዩ የመብት ጥሰቶች ተፈጽሞባቸዋል።
ከሶስት ዓመት በፊት 165 ሽህ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ከሳኡዲ አረቢያ በግዳጅ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጋቸው ይታወሳል። ምጣኔ ሃብታዊ እድገት አምጥታለች ከምትባለው ኢትዩጵያዊያ በሕገወጥ መንገድ ወደ ባሕረሰላጤው አገራት ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው የሚገቡ ኢትዩጵያዊያን ስደተኞች በየዓመቱ ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ እና በቀጠናው ስጋት እየፈጠረ መምጣቱን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይን ጠቅሶ ሪሊቭ ዌብ ዘግቧል።