በአዲስ አበባ ከተማ አሜሪካ ግቢ መኖሪያ ቤታቸው ለልማት የፈረሰባቸው ነዋሪዎች መንግስት ተለዋጭ ቦታ ለመስጠት የነበረውን ቃል አላከበረም ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ

ኢሳት (ታህሳስ 11 ፥ 2009)

በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ አሜሪካ ግቢ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ መኖሪያ ቤታቸው ለልማት ተብሎ የፈረሰባቸው ነዋሪዎች መንግስት ተለዋጭ ቦታ ለመስጠት የነበረውን ቃል አላከበረም ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ።

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሃላፊዎች በበኩላቸው ህጋዊ የመኖሪያ ማስረጃ እያላቸው ያልተስተናገዱ ነዋሪዎች የሉም ሲሉ ምላሽ መስጠታቸው ታውቋል።

ይሁንና ቅሬታን እያቀረቡ ያሉ ነዋሪዎች ህጋዊ ይዞታ እያላቸው ምትክ ቦታ ሳይሰጣቸው ለረጅም ጊዜ መቆየታቸውንና ለማህበራዊ ችግሮች ተጋልጠው እንደሚገኙ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

በዚሁ አሜሪካ ግቢ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩ በርካታ ነዋሪዎች ከወራት በፊት ለኢሳት በሰጡት ቃለምልልስ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወሰደው ዕርምጃ ከንግድ ድርጅቶቻቸው ሊፈናቀሉ መቻላቸውን ገልጸዋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩት እነዚሁ ነዋሪዎች የከተማው አስተዳደር ህጋዊ ምላሽ ሊሰጣቸው ባለመቻሉ ምክንያት ልጆቻቸው መደበኛ ትምህርታቸው መከታተል እንዳልቻሉ አስረድተዋል።

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሃላፊዎች ህጋዊ ማስረጃ ያላቸው ነዋሪዎች በሙሉ ተስተናግደዋል የሚል ምላሽን ቢሰጡም ከነዋሪዎቹ መካከል ምን ያህሉ ምትክ ቦታ እንደተሰጣቸው የሰጡት መረጃ የለም።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ሲያካሄድ የነበረው ነዋሪዎችን ለልማት የማስነሳት ፕሮግራም ለግጭት መንስዔ ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል።

ባለፈው አመት ሰኔ ወር በላፍቶ ክፍለ ከተማ ህገወጥ የተባሉ ይዞታዎችን ለማፈረስ የተካሄደ ዘመቻ ተቃውሞን አስነስቶ ለሶስት የክፍለ ከተማው ሃላፊዎችና የጸጥታ አባላት ሞት ምክንያት መሆኑ ተዘግቧል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በቦሌ ክፍለ ከተማ ስር በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የተካሄደ ዕርምጃ ከ10 ለሚበልጡ ሰዎች ሞት መንስዔ ሆኖ ነበር። የከተማዋ አስተዳደር ድርጊቱን ተከትሎ ህገወጥ የተባሉ የመኖሪያ ቤቶችን የማፍረስ ዘመቻ ለጊዜው አቋርጦ ይገኛል።

ይሁንና አስተዳደሩ ዘመቻውን በአዲስ መልክ ለመቀጠል ከነዋሪዎቹ ጋር ምክክርን እያካሄደ መሆኑን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል። በእስካሁኑ ሂደት በከተማዋ ከ20ሺ የሚበልጡ ነዋሪዎች ከይዞታቸው መፈናቀላቸውን ይነገራል።

የከተማዋ አስተዳደር በበኩሉ ከነባር ይዞታቸው የተነሱ ነዋሪዎችን መልሶ ለማቋቋም ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማን ወደ ኦሮሚያ ክልል ለማስፋፋት የተያዘው እቅድ ባለመሳካቱ ምክንያት የከተማዋ አስተዳደር ፊቱን ወደ ከተማዋ በማዞር ህገወጥ የተባሉ ይዞታዎችን ለማስለቀቅ አዲስ ዕቅድ መንደፉም ተነግሯል።