ታኅሣሥ ፲ (አሥር)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኮ/ል ዶመቀ ዘውዴን ከጎንደር አውጥቶ ለመውሰድ ከሚደረግ ሙከራ ጋር በተያያዘ በእስር ቤቱ ውስጥ በተነሳ ተቃውሞ 1 እስረኛ ሲገደል ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ እስረኞች ደግሞ ቆስለዋል። አንዳንድ ወገኖች የሟች እስረኞች ቁጥር 3 ነው ይላሉ።
ኮ/ል ደመቀን ከሌሎች እስረኞች ለይቶ በማውጣት በአንድ ክፍል ውስጥ ለማስቀመጥ የተደረገውን ሙከራ ኮሎኔሉም ሆኑ እስረኞች የተቃወሙት ሲሆን፣ ይህንን ተከትሎ ተኩስ ተከፍቶ በርካታ እስረኞች ተጎድተዋል። ኮሎኔሉን በሚጠብቁ የልዩ ሃይል አባላት እና በፌደራል ፖሊሶች መካከል ልዩነት መፈጠሩንም ምንጮች ይገልጻሉ። የእስር ቤቱ ጠባቂ የልዩ ሃይል አባላት ኮ/ል ደመቀን አሳልፈን አንሰጥም ሲሉ፣ ከፌደራል ተልከው የመጡት ወታደሮች ደግሞ ኮሎኔሉን መውሰድ ይፈልጋሉ። በሁለቱ ሃይሎች መካከል ቅዳሜ ሌሊት በነበረው የተኩስ ለውጥጥ ሶስት ወታደሮች ሳይገደሉ እንዳልቀረ ምንጮች ገልጸዋል።
ውጥረቱ ዛሬም የቀጠለ ሲሆን፣ ወደ እስር ቤቱ የሚወስዱ መንገዶች በሙሉ መዘጋታቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። በእስር ቤቱ ጠባቂዎችና በፌደራል ፖሊስ አባላት መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ተከትሎ፣ እንቅፋት ይሆናሉ የሚባሉ ታጣቂዎች ወደ ሌሎች ቦታዎች እንዲሄዱ እየተደረገ ነው። እስረኞችን እያሳመጹ ነው የሚባሉ እስረኞችም እየተለዩ በመወሰድ ላይ ናቸው። ኮ/ል ደመቀ ይህን ዜና እስካጠናከረንበት በኢትዮጵያ አቆጣጠር እስከ ቀኑ 11 ሰአት በእስር ቤቱ ውስጥ ይገኛሉ።
በሌላ ዜና ደግሞ ከሰሜን ጎንደር የታፈሱ ወጣቶችን ወደ ብርሸለቆ ለመውሰድ ዝግጅት እየተደረገ ነው። ከታሰሩት መካከል ከወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ግንባር ቀደም ሆነው ጥያቄውን ሲያሰሙ የነበሩ ወጣቶች ይገኙበታል።
ቀደም ብለው የተያዙ የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ የኮሚቴ አባላት የሽብርተኝነት ወንጀል ክስ ተከፍቶባቸዋል። ክሱ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ የችግሩ መነሻ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ናቸው በማለት ከተናገሩት ንግግር ጋር የሚጋች ሆኗል። አቶ ሃይለማርያም ቀደም ብለው ባህርዳር ላይ ባደረጉት ንግግር የሁለቱ ክልል አመራሮች ሁሉም ህዝብ የኔ ነው የማለት አስተሳሰብ የላቸውም ብለው ነበር። “ችግሩን ከመፍታት ይልቅ የግራው የኔ ነው፣ የቀኙ ያንተ ነው ፣ እየተባባሉ በጠባብነት እና የእኔ እኔ በሚል የተበከለ አመለካከት ተይዘው ችግሩ እንዳይፈታ አድረገውታል” በማለት አቶ ሃይለማርያም ቢናገሩም የኮሚቴ አባላቱ ግን ለጥያቄውና ጥያቄውን ተከትሎ ለሚነሳው ተቃውሞ ተጠያቂዎች ሆነው ቀርበዋል።