ታኅሣሥ ፲ (አሥር)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የመኸር ወቅት ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ አለመጣሉን ተከትሎ በኢሊኖ የአየር መዛባት ተጋላጭ በሆኑ የደቡብ እና ደቡባዊ ምስራቅ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ድርቅ፣ የውሃ እጥረት እና አጣዳፊ የተቅማጥ በሽታ መከሰቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ቀውስ ጥናት ቡድን አስታውቋል። በወቅታዊ የጤና ሪፖርት መሰረት በኦሮሚያ ክልል 5 ሽህ 150 ነዋሪዎች የተቅማጥ የበሽታው ተጠቂዎች እንዳሉ ግብረሰናይ ድርጅቶች ከክልሉ የጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ዝርዝር ሪፖርት አውጥቷል። በዚህም መሰረት 114 ወረዳዎች እና 13 ከተሞች ከቀናት እስከ ወራት በዘለቀው አጣዳፊ የተቅማጥ በሽታ የተጠቁ ነዋሪዎች እንደሚገኙባቸው ተለይተው ታውቀዋል።
በተለይም በምስራቅ ሃረርጌ ውስጥ የሚገኙ ሰባት ወረዳዎች፣ በምእራብ ሃረርጌ ሶስት ወረዳዎች፣ በምእራብ አርሲ ሶስት ወረዳዎች፣ በባሌ አራት ወረዳዎች፣ ሁለት የምስራቅ ወለጋ ወረዳዎች እና የሻሸመኔ ከተማ ክፉኛ የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል። በተጨማሪም በድርቁ ምክንያት ክፉኛ ለተጎዱ ለሶማሊያ፣ ደቡብ እና ኦሮሚያ ክልልም ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ እና የቤት መገልገያ ውሃ አቅርቦት በ60 ተሽከርካሪዎች በግብረሰናይ ድርጅቶች አማካኝነት እየቀረበላቸው ነው።
ከያዝነው ታህሳስ ወር ጀምሮ በዩኒሴፍ አማካኝነት የውሃ እደላ ተጠቃሚ የሆኑ አካባቢዎች ከምእራብ ሃረርጌ ዞን ጉንቢ፣ ቦርደዴ፣ሃዊ፣ ጉዲና፣ ቡርቃ ዲንቱ እና ኦዳ ቡልቱም፤ ምስራቅ ሃረርጌ ዞን የፈንታሌ እና ቦሰት ወረዳዎች፣ ከምእራብ አርሲ ዞን ሻላ ወረዳ ናቸው። እስካሁን በተደረገው የውሃ አቅርቦት እደላ 650 ሽህ የአሜሪካን ዶላር ወጪ መደረጉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ቀውስ ጥናት ቡድን በሳምንታዊ የሪፖርት ጥናቱ አመልክቷል።