ማላዊ በእስር ላይ የቆዩ ከ100 በላይ ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሃገራቸው መመለሷን አስታወቀች

ኢሳት (ታህሳስ 7 ፥2009)

ማላዊ ወደ ሃገሪቱ በህገ-ወጥ መንገድ ገብተዋል ተብለው ያለ መጠለያ በእስር ላይ የቆዩ ከ100 በላይ ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሃገራቸው መመለሷን አርብ አስታወቀች።

የአለም አቀፍ ስደተኞች ቀን አከባበርን አስመልክቶ በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫን የሰጡት የሃገሪቱ ባለስልጣናት ካለፉት ሁለት አመታት ጀምሮ ወደ ማላዊ በህገወጥ መንገድ የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

ከእነዚሁ ስደተኞች መካከል ያለበቂ መጠለያ በእስር ላይ የነበሩ ከ100 የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተያዘው አመት ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን ኒያሳ ታይምስ የተሰኘ የሃገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል።

የማላዊ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ግለሰቦች በሃገሪቱ እስር ቤቶች የሚገኙ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ያለበቂ ምግብ እና በሽታ ጉዳት እንደደረሰባቸው ነው ሲሉ ድርጊቱን ሲቃወሙ ቆይተዋል።

በአሁኑ ወቅት 120 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሶስት የሃገሪቱ እስር ቤቶች ለእንግልት ተዳርገው ይገኛሉ። የማላዊ ባለስልጣናት ስደተኞቹ ወደሃገራቸው ለመመለስ ድጋፍ እየተፈለገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የማላዊ የሃገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ቤስትን ቺሳሚል ባለፈው አመት ከ300 በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ አዲስ አበባ እንዲጓጓዙ መደረጉን አውስተዋል።

ከማላዊ በተጨማሪ በጎረቤት ታንዛኒያ ማሊ እና ሌሎች ጎረቤት ሃገራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ የአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) መረጃ የመለክታል።

ባለፈው አመት በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያን ወደ የመን፣ ሶማሊያ፣ ግብፅና ሱዳን በመሰደድ ላይ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።