ኢሳት (ታህሳስ 7 ፥2009)
ኢትዮጵያና ኬንያ ከአራት አመት በፊት የኬንያ – ላሙ ወደብን በጋራ ለማልማት ያቀዱት የ22 ቢልዮን ዶላር ፕሮጄክት የገንዘብ እጥረት አጋጠመው።
የኬንያ ባለስልጣናት በአፍርካ ግዙፍ እንደሆነ ብዙ የተነገረለት ይኸው ፕሮጄክት እስካሁን ድረስ በተጠበቀው መጠን ተግባራዊ አለመደረጉ ስጋት እያሳደረ መምጣቱን በመግለጽ ላይ መሆናቸውን ዘስታር የተሰኘ የሃገሪቱ ጋዜጣ አርብ እልት ዘግቧል።
ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና የኬንያው የቀድሞ ፕሬዚደንት ሞዋይ ኪባኪ ከአራት አመት በፊት ወደቡን በጋራ ለማልማትና የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ከወደቡ ወደ ኢትዮጵያ እንዲዘረጋ ስምምነት መድረሳቸው ይታወቃል።
ይሁንና ፕሮጄክቱ እስካሁን ድረስ ከኢትዮጵያ በኩል አነስተኛ ፍላጎት እየታየበት መምጣቱን የኬንያ ባለስልጣናት ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ ለዚሁ ፕሮጄክት ልዩ ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ፊቷን ሙሉ ለሙሉ ወደ ጅቡቲ ወደብ ማዞሯንና ድርጊቱ በኬንያ በኩል ጥርጣሬ ማሳደሩ ታውቋል።
ሁለቱ ሃገራት የደረሱትን ስምምነት ተከትሎ የኬንያ የትራንስፖርት ኤጀንሲ ከላሙ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር የሚደርስ የመንገድ ግንባታን በማከናወን ላይ ይገኛል። 22 ቢሊዮን ዶላር ይፈጃል የተባለው ፕሮጄክት ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት እንዳጋጠመው ጋዜጣው በዘገባው አስፍሯል።
የኬንያ የትራንስፖርትና ወደብ አገልግሎት ሃላፊ ሲልቪስተር ካሱኩ ኢትዮጵያ ከዚህ ሁለገብ ፕሮጄክት ራሷን ታገላለች ብለን አናምንም ብለዋል።
ይሁንና ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት አጋጥሞት የሚገኘው የላሙ የወደብ ፕሮጄክት በእስካሁኑ ቆይታው ከኢትዮጵያ በኩል በሚጠበቀውና በተደረሰው ስምምነት መጠን እየተካሄደ አለመሆኑ ተገልጿል።
በኬንያ የላሙ ወደብ ይካሄዳል የተባለው የፕሮጄክት ማስፋፋት ኢትዮጵያ አብዛኛው የገቢና የውጭ ንግዷን በወደቡ በኩል እንድታካሄድ እቅድ ተይዞለት እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።
ኢትዮጵያና ኬንያ ይህንን ግዙፍ ፕሮጄክት ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ቢደርሱም ኢትዮጵያ ከዚሁ ስምምነት በኋላ ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኝ የባቡር መስመር ግንባታ ማከናወን በኬንያ በኩል ጥርጣሬን ማሳደሩ ታውቋል።
ሁለቱ ሃገራት በጋራ ለማልማት የደረሱትን የ22 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጄክት ለመደገፍ የተለያዩ አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የብድር ድጋፍን ለማድረግ ፍላጎት ቢያሳዩም በሂደት ፕሮጄክቱ የገንዘብ እጥረት እንዳጋጠመው ዘስታንዳርድ ጋዜጣ አስነብቧል።
በኬንያ ባለስልጣናት በኩል የተነሳውን ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ኢትዮጵያ የሰጠችው ምላሽ የለም።