ኢሳት (ታህሳስ 6 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተያዘው አመት ሊያካሄዳቸው ላቀደው የማስፈፊያ ስራዎች የአፍሪካ ልማት ባንክ የ159 ሚሊዮን ዶላር ብድርን አጸደቀ።
በአፍሪካ እየታየ ያለው የመንገደኞች ቁጥር መቀነስና በሃገሪቱ ተከስቶ ያለው አለመረጋጋት በአየር መንገዱ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ብሉምበር የዜና ወኪል ከቀናት በፊት መዘገቡ ይታወሳል። እነዚህ ክስተቶች በተያዘው አመት በአየር መንገዱ ገቢ ላይ መቀዛቀዝን ሊፈጥር እንደሚችል የዜና ወኪሉ የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ አቅርቧል።
የአየር መንገዱ የ195 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለመስጠት ውሳኔ መደረሱን ሃሙስ ይፋ ያደረገው የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ብድሩ የድርጅትን የማስፋፋት እቅዶችን ለማገዝና በረራዎችን በዘመናዊነት ለማደራጀት እንደሚውል መግለጹን ሮይተርስ ዘግቧል።
ባለፈው በጀት አመት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ3.5 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡን ይፋ አድርጓል። ይሁንና የድርጅቱ ትርፋማነት በተያዘው በጀት አመት ቅነሳን ሊያሳይ እንደሚችል ብሉምበርግ አስነብቧል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በምዕራብ አፍሪካ ያለው የመንገደኞች መቀዛቀዝን ተከትሎ ከተለያዩ አካላት ያልተከፈለ 200 ሚልዮን ዶላር ገንዘብ ተይዞበት እንደሚገኝም ተመልክቷል።
ወደ 80 አካባቢ የተለያዩ አውሮፕላኖች ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ በገቢና ትርፍ ግንባር ቀደም ሲሆን፣ በቀጣዮቹ 10 አመታት አመታዊ ገቢውን ወደ 10 ቢሊዮን ለማድረስ ፕሮግራም መንደፉን ከድርጅቱ ድረገጽ ለመረዳት ተችሏል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ለአየር መንገዱ የሚሰጠውን ብድር በአፍሪካ የንግድ ኢንሹራንስና በአፍሪካ የኤክስፖርት ክሬዲት ኤጀንሲ በኩል የሚሸፈን መሆኑን ባንኩ በድረ-ገጹ አስፍሯል።