ኢሳት (ታህሳስ 5 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ባለው የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ዙሪያ ለመምከር በአሜሪካ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ረዳት ሚኒስትር ቶም ማሊኖውስኪ የተመራ የልዑካን ቡድን ረቡዕ አዲስ አበባ መግባቱ ታውቋል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሃገሪቱ ተግባራዊ የተደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ ዕርምጃው በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ስጋትን አሳድሯል ሲል በተደጋጋሚ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።
በአዲስ አበባ የሶስት ቀን ቆይታ የሚኖረው ይኸው የልዑካን ቡድን የአሜሪካ አለኝ የምትለውን የሰብዓዊ መብት ስጋት አንስቶ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክር ታውቋል።
ረዳት ሚኒስትሩ ማሊኖውስኪ በሃገሪቱ በሚኖራቸው ቆይታ ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በሃገሪቱ ጉብኝትን ሲያደርግ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል።
በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በአስቸኳይ አዋጅ ምክንያት የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ መደረጉ ስራውን በአግባቡ ማከናወን እንዳላስቻለው በመግለጽ ላይ ነው።
በኢትዮጵያ የሶስት ቀን ቆይታ የሚኖረው የአሜሪካ የሰብዓዊ መብት ልዑካን ቡድን እነዚህንንና ተያያዥ ጉዳዮችን በማንሳት ሰፊ ምክክርን እንደሚያካሄዱ ለመረዳት ተችሏል።