ታኅሣሥስ ፬ (አራት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኤሊኖ የአየር መዛባት ምክንያት በኢትዮጵያ የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ የዜጎችን ሕይወት ከርሃብ ለመታደግ 900 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወይም ከ 20 ቢሊዮን ብር ያላነሰ የገንዘብ እርዳታ እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
በምስራቅ ኢትዮጵያ በሚገኙ አካባቢዎች የኢሊኖ አየር ለውጥ በፈጠረው አሉታዊ ተጽእኖዎች ሳቢያ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ ተላላፊ በሽታዎች መዛመት እና ማኅበራዊ ቀውሶች ተፈጥረዋል። በድርቁ እና በተዛማጅ አሉታዊ ተግዳሮቶች ተጠቂ የሆኑ 9.7 ሚልዮን ኢትዮጵያዊን ዜጎች መኖራቸውን ጥናቱ አመላክቷል።
በአዲሱ ዓመት እ.ኤ.አ. 2017 የሕንድ ውቂያኖስ ሙቀት መጨመር በሚፈጥረው አሉታዊ የአየር መዛባት ምክንያት ሁኔታው በከፋ ሁኔታ ተባብሶ እንደሚቀጥል ይጠበቃል። በዚህም በመኸር የምርት ወቅት በደቡባዊ እና ምስራቃዊ የኢትዮጵያ ክፍሎች የውሃ አቅርቦት እጥረት በከፋ ሁኔታ ይከሰታል። ድርቁ በነዋርዎቹ እና በቤት እንስሶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሱ አስቀድሞ ለጋሽ ድርጅቶች ልገሳቸውን በአፋጣኝ እንዲያደርጉ ሲል ተማጽኖውን አቅርቧል።
በዓለም ላይ ለድርቅ ተጋላጭ ለሆኑ 33 አገሮች 22.2 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል። ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የገንዘብ ድጎማ እርዳታ 44 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።