ታኅሣሥስ ፬ (አራት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ማንነታቸውን የሚገልጽ ሕጋዊ መረጃ ያልያዙ ሰባት ኢትዮጵያዊያን በሩቩ ወንዝ ላይ አስከሬናቸው ተንሳፎ መገኘቱን የታንዛኒያ የአገር ውስጥ ሚንስትር አስታውቀዋል።
ሚንስትሩ ሚውጉሉ ሚቼንባ ለአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደተናገሩት የመጀመሪያ የምርመራ ውጤት እንደሚያሳየው ሟች ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በባጋማዮ አውራጃ በሚገኝ የውሃ ዳርቻዎች ተገለው ወንዙ ውስጥ ተጥለዋል። የስድስቱ አስከሬን በውሃው ላይ ተንሳፎ ያዩት የአካባቢው ነዋሪዎች ባደረጉት ጥቆማ አስከሬናቸው መገኘቱን እና ሟቾቹ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ወንዶች ሲሆኑ እድሜያቸውም ከ25 እስከ 35 ዓመት እንደሚደርስ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የሟቾቹ ቦርሳ ከአስከሬናቸው ጋር በድንጋይ ስር አብሮ መገኘቱንም መርማሪዎቹ አስታውቀዋል።
የቀጠናው የፖሊስ ኮማንደር የሆኑት ቦናሞንሹር ሙሺንጊ በበኩላቸው ወደ ታንዛኒያ በሕገወጥ መንገድ የሚገቡ ስደተኞች ሰብዓዊነት በጎደለው መልኩ የሚጓጓዙ ሲሆን በዚህም ምክንያት ብዙዎቹ መንገድ ላይ ይታመማሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ በጉዞ ላይ ይሞታሉ።
የአንዱን ኢትዮጵያዊ ስደተኛ አስከሬን ባገኙበት የወንዙ ዳርቻ ደን ውስጥ ሌሎች ክፉኛ የተጎሳቆሉ 81 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች መገኘታቸውን ዘ ሲት ዝን ዘግቧል።